በቻግኒ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

60

ባህርዳር፤ታህሳስ 282013( ኢዜአ) ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች ከአንድ ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ  የተደገውን ድጋፍ ሲያሰረክቡ እንዳሉት  ድጋፉን  ማሰባሰብ የተቻለው ከሶስት የክልሉ መስሪያ ቤቶች፣ ከክልሉ ሴቶች ፌዴሬሽን አደረጃጀቶችና ከንግዱ ማህበረሰብ ነው።

ከተደረጉት ድጋፎች መካከልም 70 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ 2ሺህ 500 ሊትር ዘይት፣ 200 ካርቶን ብስኩት፣ አልሚ ምግብ፣ አልባሳትና የተለያዩ የንፅህና መጠበቂያዎች ይገኙበታል።

በተጨማሪም ለተፈናቃዮች የገና በዓል መዋያ ከንግዱ ማህበረሰብ 5 ሰንጋዎች፣ 5 የመጠለያ ድንኳን፣ የመኝታ ፍራሾችና የማብሰያ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

"የተደረገው ድጋፍ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችን አጋርነታቸንን ለመግለጽ ነው" ያሉት ሃላፊዋ፤ በቀጣይም ሌሎች ተቋማት ድጋፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የአዊ ብሄረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን ድጋፉን ሲረከቡ እንደገለጹት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተፈናቅለው ለመጡ ወገኖች ህብረተሰቡ እያደረገ ባለው ድጋፍ ሊመሰገን ይገባል።

የተፈጠረው ችግር ተቀርፎ ተፈናቃዮች ወደ መጡበት አካባቢ እስኪመለሱ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ በማድረግ፤ አሁን ከክልሉ የተለያዩ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች የተደረገውንም ሆነ ሌሎች ድጋፎችን በአግባቡ ለተጎጂዎች መድረሱን በቅርበት ክትትል እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና ከ1ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው 7 ሰንጋዎች፣ 223 ኩንታል በሶ፣ ዳቦቆሎ፣ የገብስ ቆሎና በቆሎ ከህብረተሰቡ በማሰባሰብ ድጋፍ መደረጉን የምዕራብ ጎጃም ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ገልጸዋል።

ከመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ቢዘር ቀበሌ በደረሰባቸው ጥቃት ተፈናቅለው በቻግኒ ራንች የመጠለያ ጣቢያ ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል አቶ ሰማኝ ጌታነህ በበኩላቸው የደረሰብን ግፍና በደል ተነግሮ አያልቅም ብለዋል።

"ብዙ ችግር አሳልፈናል" ያሉት አቶ ሰማኝ አሁን መንግስትና ህብረተሰቡ ለዕለት የሚሆን የዳቦ ዱቄት፣ አልሚ ምግብ፣ አልባሳትና ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉ ጊዜያዊ ችግራቸው እንዲቀረፍ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በመተከል ዞን በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ከ60 ሺህ በላይ ወገኖች በቻግኒ የመጠለያ ጣቢያዎችና በጓንጓ ዙሪያ ወረዳ ተጠልለው እንደሚገኙም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም