በበዓል ግብይት የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ ምርቶች የማቅረብ ህገወጥነት ሊፈጸም ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል

88

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) በበዓል ግብይት ወቅት የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ ምርቶች የማቅረብ ህገወጥነት ሊፈጸም ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አሳሰበ።

ህብረተሰቡ በበዓል ግብይት ወቅት ሊፈጸሙ ከሚችሉ ህገወጥ ተግባራት መጠንቀቅ አለበት ተብሏል።

ባለስልጣኑ ለመጪዎቹ የገና እና የጥምቀት በዓላት ህብረተሰቡ ግብይት ሲፈጽም ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በበዓል ግብይት ወቅት የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉና ተመርምረው ለምግብነት እንዲውሉ ብቃታቸው ያልተረጋገጡ ግብአቶች ለገበያ በማቅረብ መጠነ ሰፊ ህገወጥነት ሊፈጸም እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በመሆኑም አምራቾችና ሸማቾች ተገቢ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በገበያ ውስጥ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን የመቆጣጠር ሥራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ህብረተሰቡ ህገ-ወጥ እርድ፣ ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀል፣ ህገ ወጥ የመድኃኒት ችርቻሮ እና ሌሎች ህጋዊ ያልሆኑ ተግባራት ሲያጋጥሙት ለሚመለከታቸው አካላት ፈጥኖ እንዲያሳውቅም ጥሪ አቅርቧል።

አምራቾች፣ የሉካንዳ ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና መድኃኒት ቤቶች ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡም ነው ባለስልጣኑ ያሳሰበው።

ህብረተሰቡ በየአካባቢው እርድ ሲያከናውንና ተረፈ ምርቶችን ሲያስወግድ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል።

በዓሉ ሲከበር ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ የጥንቃቄ መመሪያዎች እንዲተገብሩም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ህብረተሰቡ ህገ ወጥ ድርጊቶች ሲያጋጥሙት በነጻ የስልክ መስመር 8864 በመደወል ማሳወቅ እንዳለበት ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም