ኀብረተሰቡ በበዓሉ ወቅት ጤናማነቱ ካልተረጋገጠ የስጋ ምርት ጥንቃቄ ማድረግ አለበት

65

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኀብረተሰቡ በበዓሉ ወቅት ከህገ ወጥ እርድና ጤናማነቱ ካልተረጋገጠ የስጋ ምርት ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት በዓሉን አስመልክቶ በከተማዋ ህገወጥ እርድ ለመከላከልና ለኀብረተሰቡ ግንዛቤን ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ስመኘው ተሾመ በዚህ ወቅት ህገወጥ እርድ ግብርን መሰወር በሚሹ አካላት የሚፈጸም ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።   

ዘመናዊ የእርድ ስርዓትን የማይከትል በመሆኑም በቆዳና ሌጦ ምርት ላይ ብክነትና የጥራት ጉድለት እንደሚያስከትልም ጠቁመዋል።

በጤና ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑም ኀብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ነው የጠየቁት።

ኀብረተሰቡ የቄራዎች ድርጅትን በመጠቀም የእርድ አገልግሎትን ማግኘት እንደሚችልም አስረድተዋል።  

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ እንድሪስ በበኩላቸው ድርጅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ እርድ፣ የስጋ ስርጭት፣ ተረፈ ምርትና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን የሚያከናውኑ በቂ ሰራተኞች እንዳሉት ገልጸው፤ ለሰራተኞቹ አስፈላጊ የሆኑ የኮቪድ-19 ጥንቃቄ ግብአቶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ኀብረተሰቡ ያለ ሰዓት ገደብ የእርድ አገልግሎትን እንዲያገኝም በሶስት ፈረቃ 24 ሰዓት አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

35 የስጋ ማሰራጫ ተሽከርካሪዎች መዘጋጀታቸውንም ነው ስራ አስኪያጁ የገለጹት ።

ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ከ200 በላይ በሽታዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ጥንቃቄ በጎደለው እርድና ጤንማነቱ ያልተረጋገጠ ስጋን በመመገብ የሚተላለፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ምክትል ኮሚሽነር ፍቅርተ ነጋሽ ኮሚሽኑ ህገወጥ እርድ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት በተመለከተ ለኀብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ህገወጥ እርድና ዝውውር በሚያደርጉ አካላት ላይ  ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ነው የገለጹት።

ኀብረተሰቡ ህገወጥ እርድን በሚመለከትበት ወቅት በ8868 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ ማድረስ እንደሚችልም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም