በጎንደር ከተማ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን የማሻሻል ስራ እየተሰራ ነው

64

ጎንደር፣  ታህሳስ 27/2013 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በመማሪያ ግብአቶች አለመሟላት ከደረጃ በታች የሆኑ 40 ትምህርት ቤቶችን በዚህ አመት ደረጃቸውን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

ለፋሲለደስ መሰናዶ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት የዳሽን ቢራ አክስዮን ማህበር የ5 ሚሊዮን ብር የግንባታ ቁሳቁስ ድጋፍ አበርክቷል፡፡

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ የትምህርት ቤቱ የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት በተጎበኘበት ወቅት እንዳሉት በከተማው ከሚገኙ 83 ትምህርት ቤቶች 96 በመቶው የሚሆኑት ከደረጃ በታች የሚገኙ ናቸው፡፡ 

የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አመት 40 ያህሉን ደረጃቸውን ለማሻሻል አቅዶ በአሁኑ ወቅት የአራት ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ለትምህርት ቤቶቹ ደረጃ ማሻሻል የሚውል አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ከተማ አስተዳደሩ በጀት እንደመደበም ገልጸዋል፡፡ 

የአማራ ልማት ማህበርን ጨምሮ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ተቋማት በገንዘብ በቁሳቁስና በሙያቸው ለመሳተፍ ቃል መግባታቸውን በመጠቆም ዳሽን ቢራ አክስዮን ማህበር ላደረገው ድጋፍም አመስግነዋል፡፡

የዳሽን ቢራ አክስዮን ማህበር የኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ ማሩ ሙሉጌታ በበኩላቸው አክስዮን ማህበሩ ለፋሲለደስ መሰናዶ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ የአርማታ ብረቶችን ገዝቶ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡ 

አክስዮን ማህበሩ ከዚህ ቀደም በጎንደርና አካባቢው በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ፣ ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋምና ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የሚውል ከ135 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

የፋሲለደስ የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእስ መምህር አቶ እንዳለ ታደሰ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ላለፉት 79 አመታት አገልግሎት የሰጠ ነው።

ባለፈው አመት በትምህርት ቤቱ የተጀመረው የማስፋፊያ ግንባታ 30 የመማሪያ ክፍሎችና 5 የአስተዳደር ቢሮዎችን ያካተተ ነው፡፡

70 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሚጠይቀው የማስፋፊያ ፕሮጀክት በውጪ የሚኖሩ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች፤ ከተማ አስተዳደሩ፤ በጎ አድራጊ ማህበራትና የንግድ ተቋማት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ እስካሁን መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡

የፋሲለደስ የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት ባለፉት አመታት 250 ሺህ ተማሪዎችን አስተምሮ ያበቃ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም 3 ሺህ 357 ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡

በጉብኝቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፤ የወላጅ ኮሚቴ አባላት፤ የሃይማኖት አባቶች፤ የሃገር ሽማግሌዎች፤ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም