የግብጽና የሱዳን ፍላጎት ግድቡን ማስቆም፤ ካልተቻለ የግንባታውን ሂደት ማስተጓጎል ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

115

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27/2013 ( ኢዜአ) የታችኛው ተፋሰስ አገራት በሕዳሴ ግድብ ላይ የሚያሳዩት የእግር መጎተት ግድቡ ስለሚጎዳቸው ሳይሆን ግድቡን የማስተጓጎል ወይም የማስቆም ዓላማ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

በተያዘው ሳምንት የኢትዮጵያን የሕግ ማስከበር ተልዕኮ ተከትሎ የሚናፈሱ የተሳሳቱ ትርክቶች እንዲታረሙ ለአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት የማስረዳት የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። 

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሳምንቱን አበይት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የዲፕሎማቲክ ክንውኖች አስመልክተው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ከአንድ ወር መቋረጥ በኋላ ባለፈው እሁድ በሶስቱ አገራት የውጭና የውሃ ሚኒስትሮች አማካኝነት ዳግም መጀመሩን ከሳምንቱ አበይት ዲፕሎማሲያዊ ክንውኖች ጠቅሰውታል።

በድርድሩ በደቡብ አፍሪካ አስተባባሪነት በአፍሪካ ኅብረት በተሰየሙ የባለሙያዎች ቡድን የቀረበውን የድርድር ሰነድ ኢትዮጵያና ሱዳን ሲቀበሉት ግብፅ እንዳልተቀበለችው ተናግረዋል።

እስካሁን በሶስትዮሽ ድርድሩ በተደረጉ ስምምነቶች ልዩነትና አንድነቶች በባለሙያዎች እንዲቀርቡ ስምምነት መደረሱን ገልፀው፤ ዳሩ ግን የባለሙያዎቹ ቡድን ትናንት ሊያደርገው የነበረው ውይይት የሱዳን ተሳታፊዎች ባለመታደማቸው አለመካሄዱን ገልጸዋል።

በቀሪ ቀናትም ውይይቶችን አድርገው በመጪው እሁድ በሚካሄደው ድርድር እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

ለዓመታት በዘለቀው የሶስቱ አገራት ድርድር 80 በመቶ መግባባት ላይ እንደተደረሰ፤ በተለይም በውሃ አሞላል ረገድ እንደየወቅቱ ሁኔታ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት በማይጎዳ አግባብ ግድቡን ለመሙላት ኢትዮጵያ መስማማቷን አምባሳደር ዲና ገልፀዋል።

በግድቡ ላይ መሰረታዊ ልዩነቱ በግድቡ ስራ አመራርና ኦፕሬሽን ላይ እንደሆነ ገልጸው፤ አስዋን ግድብን ግብጽ ራሷ እንደምታስተዳድረው ሁሉ ኢትዮጵያም በራሷ ግድብ ስራ አመራር ላይ አትደራደርም ብለዋል።

'ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዋን መጠቀም መብቷ በመሆኑ የውሃ ተጠቃሚነት ላይ ፎርፌ አትሰጥም' ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በኦፕሬሽን ላይ ያለው የአገራቱ ፍላጎት ከዓለም አቀፍ ሕጎች ጋር የተቃረነ እንደሆነ ተናግረዋል።

የታችኛው ተፋሰስ አገራት በግድቡ ላይ የሚያንጸባርቁት ፍላጎት ግድቡ ስለሚጎዳቸው ሳይሆን በማስመሰል ግደቡን ማስቆም ወይም ማስተጓገል እንደሆነም አብራርተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ከጦርነት ይልቅ ቀደም ሲል ወደተጀመረው የድንበር ኮሚሽን ድንበር ማካለል ስራዎችን ማስቀጠል እንደምትመርጥ ገልጸዋል።

በአንዳንድ የሱዳን ባለስልጣናት በኩል ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያ ሕግ ማስከበር ላይ በነበረችበትና ሠራዊቷም ከሱዳን ጦር ጋር ባልተዋጋበት ሁኔታ በግብታዊነት አለአግባብ ገፍተው በመግባት በአርሶ አደሩ ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ሳያንስ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ እያነሱ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሁለቱን አገራት መተጋገዝ እንጂ ግጭት እንደማትሻ፤ በአንጻሩ ለትልቁ ስዕል በማሰብ ትዕግስት ብትመርጥም ሉዓላዊነቷን አትሸጥም ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻን በተመለከተ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የአውሮፓ ሕብረት ተወካይና ለሕብረቱ አባል አገራት አምባሳደሮች የሰጡትን ማብራሪያም በሳምንቱ አባይት ዲፕሎማሲያዊ ክንውን ሲሉ ጠቅሰውታል።

በዚህም ሕግ የማስከበር ዘመቻው ከተጠናቀቀ በኋላ በክልሉ መልሶ የማቋቋም ስራዎች፣ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራዎችና ያጋጠሙ ችግሮችን በግልጽ ማስገንዘባቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ አሁን የሕግ ማስከበር ዘመቻው  በመጠናቀቁ ትኩረቱ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እየተሰራ ስለመሆኑም ገለጻ እንደተደረገላቸው አንስተዋል። 

የሕግ ማስከበር ተልዕኮውን ተከትሎ የሚናፈሱ የተሳሳቱ ትርክቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ አምባሳደሮቹም ለየመንግስታቸው መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንዲያስረዱ ስለመጠየቃቸውም ጠቅሰዋል።

ከአውሮፓ ሕብረት ተወካይ ባሻገር ማብራሪያ ከተሰጣቸው የአውሮፓ አገራት መካከል የእንግሊዝ፣ የአየርላንድ፣ የስዊድንና የስዊዘርላንድ አምባሳደሮችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

አምባሳደሮቹም አገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ጠንካራ የልማት አጋርነት ማስቀጠል እንደሚሹና የተሰጣቸውን የተሳሳተ ትርክት የማረም የቤት ስራ እንደሚወጡ ቃል ስለመግባታቸው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም