ለባህርዳር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ተገባ

96

ባህርዳር፣ ታህሳስ 27/2013(ኢዜአ) የባህር ዳር ከተማን ዘመናዊነት በማሻሻል በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል መዋቅራዊ ፕላን ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን የከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ አስታወቁ።

በተዘጋጀው መዋቅራዊ ፕላን ዙሪያ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የአስተዳደሩ  ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው  እንዳሉት የመዋቅራዊ ፕላኑ ወደ ስራ መግባት ከተማዋን በሁለንተናዊ ዘርፉ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችል ነው።

በጣናና አባይ ላይ ተመስርታ የምትገኘው ባህርዳር ከተማ በመዋቅራዊ ፕላኑ የአካባቢውን ስነ ምህዳር፣ ባህል፣ የነዋሪውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም ከሀገሪቱ  እድገት ጋር የተጣጣመና የማደግ ፍጥነቷን ከግምት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ ከነዋሪውና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ መሬት ለማውረድ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመዋቅራዊ ፕላኑ ዝግጅት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር መንግስቱ አባተ በበኩላቸው መዋቅራዊ ፕላኑ አሁን ላይ ያለውን 8 ሺህ ሄክታር የከተማዋ ስፋት ወደ 200 ሺህ ሄክታር የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

ሃላፊው እንዳመለከቱት ከዋናው የከተማዋ እምብርት በመነሳት በሁሉም አቅጣጫ አምስት ማዕከላትንና ንዑስ ማዕከላትን በማስተሳሰር የተሰራው ፕላን 4 ሚሊየን ይደርሳል ተብሎ የሚገመተው  የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ነው።

በ2010 ዓ.ም ሃምሌ ወር ላይ የተጀመረው የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ስራም ከተማዋን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ  ዋልታ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

መዋቅራዊ ፕላኑን ወደ መሬት ለማውረድም የአስር  ዓመት መሰረታዊ ፕላን በማዘጋጀት ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለጎብኞች ምቹ፣ ለኢንቨስትመንትና ኮንፈረንስ ተመራጭ ለማድረግ እንደሚተገበር ተናግረዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በመዋቅራዊ ፕላኑ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አጥኝ ቡድን መሪ ዶክተር ሱራፌል መላክ  እንዳሉት ፕላኑ ሲሰራ አሁን ያለውና የቀጣዩን የህብረተሰቡ የአኗኗር ሁኔታ ከግምት ያስገባ ነው።

የእያንዳንዱን የከተማዋ አካባቢ ባህል፣ ተፈጥሯዊ እሴቱንና ጸጋውን፣ ታሪካዊ ዳራና ሌሎች መካተት የሚገባቸውን ጉዳዮች በሳይንሳዊ መንገድ መሰናዳቱን ተናግረዋል።

በከተማዋ ለብዙ ዘመናት እንደመኖራቸው አሁን ላይ የተሰራው መዋቅራዊ ፕላን ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ መሰራቱ የተለየ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ይስማው ልመንህ ናቸው።

የከተማው ነዋሪ ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ባለቤትነቱን እንዲያሳይ በመዋቅራዊ ፕላኑ ላይ ተከታታይ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ የክልሉና ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃለፊዎች፣ ምሁራንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም