ብዝሃነትነና ልዩነትን ተቀብሎ ለአንድነትና ለሰላም ማዋል ይገባል-የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት

136
አዲስ አበባ ሐምሌ 15/2010 የፈጣሪ ፀጋ የሆነውን ብዝሃነትና ልዩነት በመቀበል ለህዝቦች አንድነትና ሰላም መዳበር ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት አስታወቀ። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው 19ኛው የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ስብሰባ ዛሬ በተለያዩ መንፈሳዊ ስነ- ስርዓቶች በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል። በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የሐዋርያት ሥራዎች ማስተባበሪያ ዋና ዳይሬክተር አባ ተሾመ ፍቅሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ጉባዔው ህያው በሆነው የሰው ልጆች ብዝሃነት ትሩፋቶች ላይ አጀንዳ ይዞ ተወያይቷል። የሰው ልጆችን ልዩነትና ብዝሃነትን የሚጎዳ ማንኛውም ዓይነት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን ተሳታፊዎቹ ማውገዛቸውንም አባ ፍቅሬ ገልፀዋል። በምስራቅ አፍሪካ አገራት በሰው ልጆች መካከል ያለውን ልዩነትና ብዝሃነት እንደ ውበት በመቀበል ለአካባቢው ህዝቦች ሰላምና አንድነት መዳበር ጥቅም ላይ በማዋል ኃላፊነታቸውን ለመወጣትም የጉባኤው ተሳታፊዎች ቃል ገብተዋል። በደቡብ ሱዳን ያለው የሰው ልጆች ስቃይና መከራ እንዲያበቃ እንዲሁም ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩት የሰላም ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ቤተክርስቲያኗ የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት እንደምትሰራም ተሳታፊዎቹ አረጋግጠዋል። መንግሥታት ትምህርትንና ጤናን ጨምሮ በአጠቃላይ የማህበራዊና ኢኮኖሚያ ልማቶችን ለማፋጠን የሚያድርጉትን ጥረት  ቤተክርስቲያኗ እንደምትደግፍም አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያስተናገደችው ጉባኤ  በመንግስት፣ በህዝቡና በምዕመናን ድጋፍና በቤተክርስቲያኗ ቆራጥ ጥረት ደማቅና የተሳካ ነበር ብለዋል። በቀጣይም በአገራቱ መካከል አንድነትን ለማጠናከርና ወንድማማችነትን ለማጎልበት ቤተክርስቲያኗ የበለጠ ትሰራለች ብለዋል። በጉባዔው ካርዲናል ብርሃነየሱስን በመተካት አዲስ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ብጹኡ አቡነ ቻልስ ካሴንዴ እንዳሉት በህዝቦች መካከል ልዩነት እንዲኖር የሚደረግ ጥረት  መወገዝ ያለበት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ቤተክርስቲያኗ የሰው ልጆች ክብር፣ ሰብዓዊነትና ሰላማዊ አንድነት እንዲኖር እንደምትሰራ ጠቁመው ሥራ አጥነትን፣ ሙሰኝነትን፣ ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን ለማስወገድ ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የምትሰራ መሆኗንም ገልጸዋል። ዘጠኝ የምስራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት ያሉት የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤ በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ይህንን ጉባኤ ኢትዮጵያ ስታስተናግድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ህብረቱ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳና ዛምቢያን በአባልነት ሲያቅፍ ሶማሊያና ጅቡቲ ደግሞ ተባባሪ አባላት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም