የአዲስ አባበን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት መስራት እንደሚገባ ተመለከተ

66
አዳማ አምሌ 15/2010 የአዲስ አባበን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ መደራሻዎችና አገልግሎቶች ላይ መስራት እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ አራተኛው የአዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ጉባኤ ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል። በከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ትራንስፖር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት የከተማዋ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ የዘርፉን ልማትና እድገት ለማዘመን በዘርፉ አዋጭ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባ አመልክተዋል። የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪን አቅም በማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጥና የቱሪስት መዳረሻዎች ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። በቱሪዝም ፖሊስ ደህንነት፣የገበያ አዋጭነትና የመዳረሻዎች ማስፋፊያ ልማትና እድገት ላይ የዜጎች ተሳትፎ የላቀ እንዲሆን በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል። የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በበቂ ሁኔታ ለማስፋፋት ነባሩንና አዳዲስ መዳረሻዎችን ለማልማት ስትራቴጅክ እቅድ ተቀርጾ እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ  አቶ ገብረጻዲቅ ሐጎስ ናቸው። የመዲናዋ የቱሪዝም ሀብት የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲኖረው  ነባሩን ማደስ፣አዳዲሶቹን ማልማትና መጠበቅ ላይ ትኩረት መስጠታቸውን አስረድተዋል። ከ400 በላይ ጥንታዊ ሆቴሎችና ሃውልቶችን ጨምሮ ነባር የቱሪዝም ቅርሶች ታሪካዊ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲታደሱና ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው  አራት ሀውልቶች በ19 ሚሊዮን ብር ሙሉ ጥገና እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል። ኃላፊው እንዳሉት የዘርፉን ልማትና ዕድገት ለማፋጠንና መዋቅራዊ ሽግግር ለማድረግ በመንግስትና የግሉ ዘርፍ እየተከናወኑ ካሉት ሆቴልና ቱሪዝም በተጨማሪ ከ8ሺህ በላይ አስጎብኝዎችን ተሳትፎና ሚና ለማሳደግ እየተሰራ ነው ። አዳዲስ የቱሪስት መደራሻዎችን ማልማት በተለይም የእንጦጦ ቱሪስት ማዕከል ለመገንባት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ  ፕሮጀክቱ በመንግስት ተቀባይነት አግኝቶ ለተግባራዊነቱ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። "የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማዘመን አንዱ በሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍረት እየተደረገ ባለው ጥረት ከ18ሺህ በላይ ሙያተኞችን በእውቀት፣ክህሎትና አቅም የማብቃት ሥራ ሠርተናል "ብለዋል። በዚህም የሆቴሎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ደረጃ እንዲጠበቅ አስችሏል ተብሏል። በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀት አራተኛው የአዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ጉባኤ በ2010 በጀት ዓመት  የሥራ ክንውንና በተያዘው  ዘመን   እቅድ ላይ  ውይይይ እያካሄደ ነው፡፡ በጉባኤው ከአዲስ አበባ አስተዳደር ከተለያዩ አደረጃጀቶችና ከፌዴራል መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ አካላት እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም