በጉራጌ ዞን ዘንድሮ ከ122 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተከላ በመከናወን ላይ ነው

69
አዲስ አበባ ሐምሌ 15/2010 በጉራጌ ዞን በተያዘው ክረምተ  ከ122 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል እንቀስቃሴ መጀመሩን የዞኑ አስተዳዳር  አስታወቀ። በጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር አስተባባሪነት የሚከናወነው ዓመታዊ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ለስድስተኛ ጊዜ በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ተካሂዷል። መርሃ-ግብሩ ''ጉዞ ወደ አረንጓዴ ልማት ዘመቻ'' በሚል መሪ ሀሳብ  ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በዘቢዳር ተራራና ዙሪያ በተመረጡ ተፋሰሶች ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት ችግኞች ሲተከሉ ቆይተዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት በማህበሩ አስተባባሪነት በዞኑ ከ100 ሺህ በላይ ችግኞች ተተክለዋል። በዘንድሮው ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ላይ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች ተሳትፈዋል። የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታጁ ነስሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በዚህ ዓመት በዞኑ ከ122 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመላው ዞኑ ለመትከል እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል። ''የዞኑ አብዛኛዎቹ ወረዳዎች የጎርፍና ተያያዥ ችግሮች ሰለባ ነበሩ፤ በዘላቂ የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴው አማካኝነትም እነዚህ ችግሮች እየተፈቱ ናቸው" ብለዋል። እንዲያም ሆኖ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴው በአከባቢው ህብረተሰብ  ያለው የባለቤትነት ስሜት ደካማ መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም ለማስተካከል የአከባቢ ዕድሮችን፣ ወጣቶችንና ባለሀብቶችን በማስተባበር ልማቱን በዘላቂ መንገድ መንከባከብ የሚቻልበት ስርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል። ጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር በየዓመቱ በሚያከናውነው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ከ1 ሺህ 200 በላይ የዞኑ ተወላጆችን ከአዲስ አበባ ወደ ቦታው እያንቀሳቀሰ ከገጠሩ ማህበረሰብ ጋር በማቀናጀት በአረንጓዴ ልማት ተግባር ያሳትፋል። የማህበሩ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት፤ በመርሃ-ግብሩ አማካኝነት ባለፉት አምስት ዓመታት  ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ጸድቋል። ''ዘንድሮ በተለይ ወጣቱ በልማት ተግባር ለመሳተፍ እየተነሳሳ ነው'' ያሉት አቶ ርስቱ የአከባቢው ወጣቶች ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሆን የሚተከሉት ችግኞች ለውጤት እንዲበቁ የጋራ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል። መርሃ-ግብሩ ከችግኝ ተከላ ባሻገር ከዞኑ ውጭ የሚኖሩ ተወላጆችን አንድነትና ትስስር እንዲሁም በጋራ የመስራቱ ባህል እንዲጠናከር የራሱን አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ገልፀዋል። በማህበሩ አስተባባሪነት ባለፉት አምስት ዓመታት በዞኑ ከ100 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን የተናገሩት ደግሞ የቦርዱ ሥራ አመራር ሊቀ-መንበር አምባሳደር ፋንታሁን ኃለሚካኤል ናቸው። የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ፈርጀ ብዙ ጉዳት መከላከል እንደሚገባ ጠቅሰው ማህበሩም አረጓዴ ልማት ስራዎች ላይ በስፋት በመሳተፍ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል። በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ለስድተኛ ጊዜ ዘንድሮ በተከናወነው ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር 25 ሺህ የዛፍ ችግኞች ተተክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም