ታላላቅ ተቋማት የፋይናንስ ሪፖርታቸውን በአዲስ አሰራር እንዲያቀርቡ በትኩረት እየተሰራ ነው -የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ

164
አዲስ አበባ ሐምሌ 15/2010 በአገሪቷ የሚገኙ ተቋማት የ2010 ዓ.ም የፋይናንስ ሪፖርታቸውን ዓለም አቀፍ  መስፈርትን/IFRS/ ባሟላ መልኩ እንዲያቀርቡ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አስታወቀ። ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት በአንድ አይነት አሰራር ሪፖርት የሚያቀርቡበትና የሚያዘጋጁበት ወጥ የሆነ የአሰራር ዘዴ ነው። አንዳንድ ተቋማትም በዚህ በአዲሱ አሰራር ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ማቅረብ መጀመራቸውን ቦርዱ ገልጿል። የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሼ የማነ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ በአገሪቷ የፋይናንስ ተቋማት የሂሳብ አያያዝ፣ ኦዲትና ሪፖርት አቀራረብ ላይ ሰፊ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። በአገሪቷ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት የሂሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ ወጥነት የሌለውና ዓለም አቀፍ መስፈርቱን የሚያሟላ ባለመሆኑ ለተለያዩ የሃብት ብክነት ሲያጋልጥ መቆየቱን ገልጸዋል። ችግሩን ለማስተካከል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 847/2006 የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ዓለም አቀፍ መስፈርቱን ያሟላ መሆን እንደሚገባ ድንጋጌ በማውጣት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል። በወጣው አዋጅ መሰረትም ትልልቅ የፋይናንስ ተቋማት  ከሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ዓለም አቀፍ የሪፖርት አቀራረብን በተከተለ መልኩ እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ መሆኑን ገልጸዋል። በዚሁ መሰረትም ጉልህ የህዝብ ጥቅም የሚሰጡ ባንኮች፣ የፌዴራል የልማት ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት በአሰራሩ መሰረት የ2010 ዓ.ም ሪፖርታቸውን በዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ አሰራር መሰረት ማቅረብ ጀምረዋል ነው ያሉት። ሪፖርቱን በዚህ መልክ ማቅረቡ ለሪፖርት አቅራቢ ተቋማት የሚኖረው ጠቀሜታም ላቅ ያለ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። አሰራሩ በዋናነት ግልዕነትና ተጠያቂነትን በማስፈን፣ የአገሪቱን ሃብት ከብክነት ከማዳን እንዲሁም የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ለማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሌሎች ተቋማትም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 መጨረሻ ድረስ ወደ ስርዓቱ እንዲገቡ የጊዜ ገደብ እንደተቀመጠላቸው ገልጸዋል። እነዚህ ደረጃዎች በአገሪቷ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምሩ ታክስና ግብርን በትክክል ለመሰብሰብና ቁጥጥር ለማድረግም  ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል። በተጨማሪም  የውጭ አገሮች ኢንቨስተሮችም  በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። ተቆጣጣሪ ተቋማቱ ከስራቸው የሚገኙ ተቋማትን የሚቆጣጠሩ ሲሆን የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተቋማቱ አሰራሩን ስለመተግበራቸው ክትትል ያደርጋልም ብለዋል። አተገባበሩ በሶስት ደረጃ የሚካሄድ ሆኖ  ልልቅ የህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት፣ የህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ እንዲሁም የምርት ገበያ ባለስልጣን የመሳሰሉ ተቋማት ሪፖርታቸውን በአዲሱ አሰራር የሚያቀርቡ ይሆናል። በሁለተኛ ዙር ደግሞ የክልል የልማት ድርጅቶች ወደ አሰራሩ የሚገቡ ሲሆን፤  በሶስተኛው ዙር ትንንሽ  የፋይናንስ ተቋማት እስከ 2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ ድረስ ማቅረብ እንደሚጀምሩ የወጣው አዋጅ በግልጽ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም