ታላቁ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡትን ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ሲቀበሉት ግብፅ ሳትቀበለው ቀርታለች

73

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ ባካሄዱት የሶስትዮሽ ስብሰባ ላይ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡትን ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ሲቀበሉት ግብፅ ሰነዱን እንደማትቀበል መግለጿን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በዛሬው እለት በበይነ መረብ የተካሄደውን የሦስትዮሽ ውይይት አስመልክቶ የተሰጠውን ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል:

የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት በበይነ-መረብ ስብሰባ አካሂደዋል።

ስብሰባው በደቡብ አፍሪካ የዓለምአቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ተካሂዷል።

ሚኒስትሮቹ የሕዳሴው ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ያደረጉ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ላይ በማተኮር ምክክር ተደርጓል፡፡

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ባለሙያዎቹ የቀረጹትን ሰነድ በበጎ እንደምትመለከተው እና በቀጣይ በሚካሄደው ድርድር ሰነዱን እንደግብዓት ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡

የሱዳን ወገን በበኩሉ ሰነዱን ለሂደቱ ጠቃሚ አድርጎ እንደሚመለከተው እና በቀጣይ የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ተጨማሪ ሚና ላይ ቢጋር በማጽደቅ ድርድሩን መቀጠል እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡

የግብጽ ወገን ሰነዱን ጨርሶ እንደማይቀበለው ገልጿል፡፡

የሕዳሴው ግድብ ሙሌት እና ዓመታዊ አስተዳደርን የሚመለከተው ሰነድ ላይ የሚደረገው ድርድር በአመዛኙ መግባባት የተደረሰበት ቢሆንም፣ ወደፊት በዓባይ ተፋሰስ ላይ በሚገነቡ የውሃ ልማት ሥራዎች ጋር የሚኖረው ቁርኝት ዋነኛ የልዩነት ሃሳብ ነው፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ፍጆታ የሌለው የኃይል ማመንጫ ግድብ እንደመሆኑ በግድቡ ላይ የሚደረሰው ስምምነት ይህንኑ ከግምት ያስገባ እና የተሟላ የውሃ ስምምነት በሌለበት እና ኢፍትሃዊ አጠቃቀም በሰፈነበት ተፋሰስ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት የሚያቅብ እንዲሆን ኢትዮጵያ አትፈቅድም፡፡

ይህን መሰረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ አሞላል እና ዓመታዊ አስተደዳር የሚመለከተውን ደንብ በጋራ ስምምነት ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ ናት፡፡

በዚህም መሰረት የስምምነት አማራጮችን ለግብጽ እና ሱዳን ወገን ያቀረበች ሲሆን የሃገራቱ ምላሽ ቀና እንደሚሆን ተስፋ ይደረጋል፡፡

በቀጣይ የሃገራቱ ባለሙያዎች በውሃ ሚኒስትሮች አመራር ስር ስብሰባቸውን በመቀጠል ስምምነት የተደረሰባቸውን እና የልዩነት ሃሳቦችን በመለየት በቀጣይ ዕሁድ ጥር 01 ቀን 2013 ለሚካሄደው የስድስት ሚኒስትሮች ስብሰባ ውጤቱን ያቀርባሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም