በመዲናዋ በተቋማት የሀብት አስተዳደር ከፍተት መኖሩን አረጋግጫለሁ-ኢንስትቲዩቱ

96

አዳማ፣  ታህሳስ 25/2013 (ኢዜአ) የአገልግሎት አሰጣጣቸው ከከተማዋ ህብረተሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር የተቆራኘ ተቋማት ላይ የአሰራርና የሀብት አስተዳደር ክፍተት ማግኘቱን የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ፣በእሳት አደጋና ስራ አመራር ፣በኢንቨስትመንት ፣የመንግስት ግዥ ኤጄንሲና ስርዓተ ፆታ ማከተቻ ላይ በዘንድሮ ዓመት የተካሄዱ ጥናቶችን በግብዓት ለማዳበርና ወደ ስራ ለማስገባት ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ መክሯል።


የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃርጋሞ ሃማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት የአገልግሎት አሰጣጣቸው ከከተማዋ ህብረተሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር የተቆራኘ ተቋማት ላይ ጥናት ተካሂዷል።


በጥናቱ የተቋማቱ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ አሰራር፣ የሃብት አስተዳደርና አያያዝ ላይ ያሉ ከፍተቶች መገኘታቸውንና መለየታቸውን ተናግረዋል።


ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ከማሳካት አኳያ በከተማዋ ያሉ መንግስታዊ ተቋማት የህብረተሰቡን የአገልግሎት ፍላጎት ማሟላት በሚችሉት ደረጃ አሰራር እንዲዘረጉ የሚያስችል ግብዓት በጥናትና ምርምር ለይቶ ለህግ አውጭውና ለተቋማቱ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።


በከተማዋ የመንግስት የጥቅል ግዥ አገልግሎት ለተቋማቱ ገዝቶ በሚያቀርበው እቃዎች ላይ ከተጠቃሚዎች በተለይ ከእቃዎች ጥራትና ጊዜ አንፃር ሰፊ ቅሬታ እየቀረበበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።


በእሳት አደጋና ስራ አመራር ኮሚሽን የሀብት አስተዳደርና አያያዝ፣ ከከተማዋ እድገት ጋር የሚመጥን አቅም ከማጎልበት አንፃር ያለበትን ክፍተት የለየ ጥናት መካሄዱንም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።


በተቋማቱ የህዝቡን የመጠቀም ፍላጎት ብሎም ጥያቄዎችን መመለስ የሚችሉ አሰራርና አደረጃጀቶች መዘርጋት እንደሚያስፈልግ በጥናት መመልከቱን ጠቅሰዋል።


"በቀጣይ በማህበራዊ ዘርፍ በጎዳና ተዳዳሪዎችና ሴተኛ አዳሪዎች ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ጥናት ይካሄዳል" ያሉት አቶ ሃርጋሞ በሌሎች የኢኮኖሚ ሴክተሮች ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር እንደሚካሄድም አመላክተዋል።

በኮሚሽኑ የጥናቱ ቡድን መሪ አቶ ተገኝ ገበያው በበኩላቸው "ዘንድሮ የተካሄዱ ጥናቶች በቀጣይ ስትራቴጅክ እቅድ፣ በከተማዋ የአገልግሎት ሴክተርና መልካም አስተዳደር፣ የሰው ሃይል ልማት ላይ በስፋት ጥናት ለማካሄድ የሚያስችሉን መነሻ ግብዓቶች ተገኝቶባቸዋል" ብለዋል።


ከአገልግሎት ሰጪ ሴክተሮች ባለፈ ጥናት የተካሄደበት የኢንቨስትመንት ዘርፉ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ከማበረታተትና ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር አንፃር ያለበት ክፍተት በጥናት መዳሰሱን ጠቅሰዋል።


በቀጣይ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፣ የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት፣ የመስተዳደሩ መንግስታዊ መዋቅር አፈፃፀም፣ አደረጃጀትና አሰራር ላይ ጥናት እንደሚካሄድ አመላክተዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኅላፊ አቶ ሃይሉ ሉሌ በበኩላቸው "የከተማዋ ህብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ የአገልግሎትና መሰረተ ልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት ኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማማከር አገልግሎቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብለዋል። 


የመስተዳደሩ የሴክተር መስሪያ ቤቶች አሰራርና አደረጃጀትና የህግ ማእቀፎቻቸውን እንዲፈትሹና መከለስ የሚያስፈልጋቸውን ደግሞ እንዲመለከቱት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም