በትምህርት ተቋማት ሰላምን ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ምንም ነገር ሊኖር አይገባም-የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት

72

ደብረ ማርቆስ፣ ታህሳስ 25/2013 (ኢዜአ )- በትምህርት ተቋማት ሰላምን ጥያቄ ውሰጥ ሊያስገባ የሚችል ማናቸውም ነገር ሊኖር አይገባም ሲሉ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ አስታወቁ።

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ''ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም'' በሚል መሪ ሀሳብ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በወቀቱ እንደገለጹት  የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር  ሂደት የማስፈንና በእውቀት የታነጸ መልካም ዜጋ የማፍራት ኅላፊነት አለባቸው።

"በተቋማቱ ሰላምን ጥያቄ ውሰጥ ሊያስገባ የሚችል ማናቸውም ነገር ሊኖር አይገባም" ብለዋል።

በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ከተማሪዎች ጋር በሚገጥሙ ጉዳዮች በግልፅ ውይይትና ምክክር በማድረግ በሰለጠነ አግባብ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

"ባለፉት አመታት ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ በተሻለ አንጻራዊ ሰላም ነበረው"ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዩኒቨርሲቲው ወደ ፊትም ምንም አይነት የፀጥታ ችግር ሳይፈጠር ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር እንደሚደረግ አመላክተዋል።

የሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም ፕሮጀክት አስተባባሪና የሰላምና የባህል ተመራማሪ  ዶክተር ወሰን ባየ በበኩላቸው "በዩኒቨርስቲዎች በተማሪዎች መካከል መተጋገዝና መተባበር እንዲኖር ሁሉም መስራት አለበት" ብለዋል።

በዩኒቨርስቲዎች የሰላም ኮንፈረሶች መካሄዳቸው ተማሪዎችም ሆነ ሌላው ማህበረሰብ ችግሮች እንዳይከሰቱ እንዲከላከልና ከተከሰቱም ቶሎ መፍትሄ ለመስጠት እንዲቻል ግንዛቤዎች እንደሚፈጥሩ አመልክተዋል።

"ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው ሲመጡ አላማቸው መማርና መማር ብቻ እንጅ ሁለት አጀንዳ ይዘው መምጣት የለባቸውም " ያሉት ተመራማሪው  ተማሪዎች በእውቀት፣ በመረጃና በምክንያት የተደገፉ ሃሳቦችን ማንሸራሸር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዘበዋል።

"የሰላም ኮንፈረሶች መካሄዳቸው የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍትሔ ለመስጠት መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራሉ" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ፀሐፊ ሀጂ መሱድ አደም ናቸው።

ዩኒቨርስቲዎች የአእምሮ ማዳበሪያ፣ ማበልጸጊያ፣ የምርምርና የእውቀት መፍለቂያ ተቋም ብቻ እንዲሆኑ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ተቋማቱ በሰላም ዙሪያ ለሚሰሯቸው ስራዎች የሃይማኖት ጉባኤ ተቋማት እገዛ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

የዩኒቨርስቲው አራተኛ አመት ተማሪ እይላቸው ተሻለ "በአብዛኛው በተማሪዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች አጀንዳውን የሚያራምደው አካል ማን እንደሆነ ሳይታወቅ የሚፈጠሩ ናቸው" ብሏል።

" በዩኒቨርስቲዎች መሰል የሰላም ኮንፈረሶች ቢሰጡ ተማሪዎች ከግጭት ተጋላጭነት ይድናሉ " ያለው ተማሪ እይላቸው ኮንፈረንሱ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስቀጠል አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጿል።

በኮንፍረንሱ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች ጨምሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተወከሉ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም