ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን ግባችን በመጨረስ ለአገልግሎት ማብቃት ነው ---ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ

84

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25/2013( ኢዜአ) በአዲስ አበባ ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን ግባችን በመጨረስ ለአገልግሎት ማብቃት ነው ሲሉ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የላፍቶ የአትክልትና ፍራፍሬ ማዕከል እንዲሁም የጀሞ እና የፉሪ የሴቶች ሁለገብ የገበያ ማዕከላትን ዛሬ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።


ምክትል ከንቲባዋ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት ከ30 እስከ 40 በመቶው የሀገሪቱ ንግድ የሚካሄድባት አዲስ አበባ ከዚህ በፊት ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት አልነበራትም።

ይህን ክፍተት ለመሙላት የላፍቶ የአትክልትና የፍራፍሬ የገበያ ማዕከል እንዲሁም የጀሞ እና የፉሪ የሴቶች ሁለገብ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን ነው የገለጹት።

ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን ግባችን በመጨረስ ለአገልግሎት ማብቃት ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ለዚህ ደግሞ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

"አዲስ አበባ ከዚህ በኋላ በየሁለት ሳምንትና በየወሩ የሚመረቁ ፕሮጀክቶች ይኖሯታል" ሲሉም አረጋግጠዋል።

የላፍቶ የአትክልትና የፍራፍሬ የገበያ ማዕከልን በአጭር ጊዜ ስናጠናቅቅ ብዙ ልምድና ትምህርት ተገኝቶበታል ብለዋል።

እነዚህ የገበያ ማዕከላት መገንባታቸውና ሥራ መጀመራቸው እናቶችና ወጣት ሴቶች የንግድ እንቅስቃሴው ውስጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።  

በጀሞ እና ፉሪ አካባቢ የተቋቋሙት የገበያ ማዕከላት የተለያዩ የግብርና ምርቶች የሚቀርቡባቸው በመሆኑ የእህል እጥረት ችግር እንዳይኖር ያደርጋሉ ተብሏል።

በዛሬው እለት የተመረቁት ሦስቱ የገበያ ማዕከላት ከ3 ሺህ 100 በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ታውቋል።

የላፍቶ የአትክልትና ፍራፍሬ የገበያ ማዕከል በከተማ አስተዳደሩ 1 ቢሊዮን ብር በጀት የተሰራ ሲሆን ለችርቻሮ 504 ሱቆች ለጅምላ ደግሞ 52 በድምሩ 556 ሱቆች አሉት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም