ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የጤና ኤክስቴንሽን ወሳኝ ሚና እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ

73

ጎባ፣ ታህሳስ 25/2013( ኢዜአ ) የግልና አካባቢ ንጽህናን በአግባቡ በመጠበቅ የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቀነስ ለጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም የተሰጠው ትኩረት ውጤት እያመጣ መሆኑ ተመለከተ፡፡

የግልና የአካባቢ ንጽህናን ጨምሮ 19ኙ የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን ተግባራዊ ያደረጉ ከ900 የሚበልጡ ግንባር ቀደም ቤተሰቦች ትናንት በባሌ ጎባ ተመርቀዋል።

በፕሮግራሙ ታቅፈው ባገኙት እውቀት የግልና የአካባቢያቸውን ንጽህና በመጠበቅ ከዚህ በፊት ከንጽህና ጉድለት ምክንያት ያስቸግራቸው ከነበሩ በሽታዎች መገላገላቸውንም ግንባር ቀደም ቤተሰቦች ገልጸዋል።

በግንባር ቀደም ቤተሰቦች ምረቃ ላይ የጎባ ከተማ የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መህፉዛ ጀማል እንደገለጹት በከተማዋ በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካኝነት ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው መርሃ-ግብር የህብረተሰቡ የጤና አጠባበቅና አመለካከት እየተሻሻለ መጥቷል።

በዚህም የግልና አካባቢ ንጽህናን ጨምሮ ሌሎች የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን በግላቸው ተግባራዊ የሚያደርጉ ቤተሰቦች እየተበራከቱ መምጣቸውን ገልጸዋል።

ፕሮግራሙን በተሻለ ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ግንባር ቀደም በመሆን ለምረቃ የበቁት ከ900 የሚበልጡ ቤተሰቦች የዚሁ ጥረት አካል ናቸውም ብለዋል፡፡

የጎባ ከተማ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ በበኩላቸው “መንግስት በሽታን መከላከል ላይ ያተኮረ ህብረተሰብን ማዕከል ያደረገ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ ነው" ብለዋል፡፡

“በተለይም የግልና አካባቢ ንጽህናንን ተግባራዊ በማድረግ መሰረታዊና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሴቶች የልማት ሰራዊት ሚና የላቀ ነው” ብለዋል።

ግንባር ቀደም ቤተሰቦቹ ለምረቃ የበቁት ኮሮናን ጨምሮ 19ኙ የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን ትርጉም ባለው መልኩ በመጠቀማቸውና ስራ ላይ በማዋላቸው መሆኑም ተገልጿል፡፡ 

ከተመራቂዎች መካከል ወይዘሮ ፋጡማ ሀጂ ማህሙድ እንዳሉት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ባገኙት ትምህርት የግልና አካባቢ ንጽህናቸውን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ በመጀመራቸው ከተላላፊ በሽታዎች እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለመታደግ ችለዋል።

ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ያጋጥሙ የነበሩና ከንጽህና ጉድለት ይከሰቱ የነበሩ የጤና ችግሮች ዛሬ ላይ መቃለላቸውንም ወይዘሮዋ ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ማብቂያ ላይ የግንባር ቀደም ቤተሰቦች ግቢ የተጎበኘ ሲሆን የእውቅና ሰርትፊኬትም ተሰጥቷቸዋል፡፡ 

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መሰረታዊ ፍልስፍና በሰለጠኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የጤና መልዕክቶችና ተግባራት ወደ እያንዳንዱ ቤትና ቤተሰብ በማድረስ የህብረተሰቡን ንቃተ ጤና በማሳደግ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም