የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራቸውን በተጠናከረ መልክ እያከናወን ነው --የምስራቅ ሐረርጌ ወጣቶች

82
ሐረር ሀምሌ 14/2010 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራቸውን በተጠናከረ መልኩ በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ። በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እስካሁን ድረስ 50 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውም ተመልክቷል። በዞኑ ሜታ ወረዳ ጨለንቆ ከተማ ነዋሪና በማርኬቲንግ የትምህርት መስክ የተመረቀው ወጣት አቢቲ መሀመድ በአሁኑ ወቅት ከ20 ለሚበልጡ ህጻናት የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል። "በክረምቱ ወጣቶች ተሰባስበን ደም ለግሰናል፤ የከተማ ጽዳትና የችግኝ ተከላ ስራም አከናውነናል፤ ይህ የክረምት በጎ ፍቃድ ስራ ወጣቱን በተለያዩ የልማት ስራ ላይ እንዲሳተፍ ስለሚያደርግ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብሏል። በሐረማያ ከተማ የሚኖረው ወጣት አህመድ ኢብራሂም በበኩሉ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች የዛፍ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ወደገጠር በመሄድ የአቅመ ደካማ ሰዎችን መኖሪያ ቤት እያደሱና እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል። እሱም በተመደበበት የከተማ ጽዳት ሥራ ወጣቶችን አስተባብሮ እየሰራና በእዚህም ደስታኛ መሆኑን ገልጿል። "ጊዜው የመደመር ነው" ያለው ወጣቱ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመጡ ተማሪዎች ህብረተሰቡን በኤች አይ ቪ ኤድስ፣ በስነ ተዋልዶ፣ በመንገድ ትራፊክ ህግ፣ በሰላምና በመሳሰሉት ጉዳዮች በማስተማር ላይ መሆናቸውንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። የዞኑ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ቦንሲቱ ኢብራሂም በበኩላቸው ዘንድሮ  ለሁለት ወራት በሚቆየው የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራ በዞኑ ከ4 መቶ ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ወጣቶቹ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው በሚሰጡት አገልግሎትም 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የልማት ሥራዎችን ያከናውናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። በተያዘው የክረምት ወራት በዞኑ ይተከላሉ ተብለው ከተዘጋጁት 120 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞች መካከል እስካሁን 50 ሚሊዮን ችግኞች በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች መተከላቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ አህመድ ናቸው። ያልተተከሉ ቀሪ ችግኞችንም ወጣቱንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ ለመትከል በአሁኑ ወቅት የዝግጅት ሥራው መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም