በሌላ አካል ጫና እና ማስፈራሪያ ተገደን ለእኩይ አላማው መሰለፍ ችለናል- በመተከል ዞን በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂዎች

91

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25/2013( ኢዜአ)  በሌላ አካል ጫና እና ማስፈራሪያ ተገደው ለእኩይ አላማ መሰለፋቸውን በመተከል ዞን ዜጎችን በመግደል ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂዎች ተናገሩ።

ከሰሞኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለንና በቆጂ ወረዳዎች ታጣቂዎች በዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈፀማቸው ይታወሳል።

ከታጣቂዎቹ መካከል በትናንትናው እለት 17ቱ በህዝቡ ትብብር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሽፍቶች መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ እንዳሉት ለዚህ እኩይ አላማ የተሰለፉት በሌሎች አካላት ጫና እና አስገዳጅነት ነው።

"በግዳጅ በድብደባና እንገድላችኋላን" ተብለን ለመታጠቅ ተገደናልም ብለዋል።

ለጥፋት የመለመሏቸው አካላት ብዙም ሳያሰለጥኗቸው የሚነግሯቸውን ሁሉ እንዲፈፅሙ ትእዛዝ እንደሰጧቸውም ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጸረ ሽምቅና ልዩ ጥበቃ አድማ ብተና መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር ዶሳ ጎሹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ታጣቂዎች ዜጎችን ሲገድሉ ከነበሩት መካከል መሆናቸው ተረጋግጦ ነው ብለዋል።

እነዚህ የታጠቁ ሽፍቶች ከዞኑ ከዳንጉር፣ ከድባጤ፣ ከቡለንና ከማንዱራ ዙሪያ የመጡ መሆናቸውንም ነው የሚናገሩት።

በአካባቢው ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል የጸጥታና ህግ የማስከበር ስራውን ተረክቦ የተጠናከረ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ኮማንደሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም