ከነገ ጀምሮ 35 ሺህ ወጣቶች በኢትዮጵያዊ አብሮነትና አንድነት ዙሪያ ስልጠና ሊወስዱ ነው

121

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25/2013( ኢዜአ) በኢትዮጵያ አንድነትና አብሮነት ዙሪያ ከነገ ጀምሮ ለ35 ሺህ ወጣቶች ስልጠና የሚሰጥ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ። 

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ አባላት አመራሮች በቢሾፍቱ ከተማ ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንዳሉት በኢትዮጵያ አንድነት እና አብሮነትን ለማጠናከር የሚያግዙ የወጣቶች ስልጠና ነገ ይጀመራል። 

የመጀመሪያ ዙር ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ 35 ሺህ ወጣቶችም ከነገ ጀምሮ በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ተዘጋጁ የማሰልጠኛ ማዕከላት ይገባሉ ብለዋል።

ለ45 ቀናት ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ለአሥር ወራት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመሰማራት ለማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሏል።

የተጀመረውን የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሥራ ከግብ ለማድረስ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ መስራት አንዱ  መሆኑንም ጠቁመዋል።

አገር ወዳድና ምክንያታዊ የሆኑ ወጣቶችን በመገንባት ሂደት ከዚህ በፊት ትልቅ ጉድለት እንደነበር ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።

ይህም በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ እርስ በእርስ ካለመተዋወቁ ባለፈ የአገሩን እሴትና ሃብት በአግባቡ ሳይረዳ ኖሯል ብለዋል።

በመሆኑም ወጣቶች ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮና ማህበራዊ እሴቶች በአግባቡ ተገንዝበው ለጋራ አገር ግንባታ በትብብር መቆም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ለዚህም በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መሰረታዊ ስልጠና መስጠት ማስፈለጉን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ስልጠናው ከትምህርት ስርአቱ ጋር ተሳስሮ የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም