በምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀናጀ የአንበጣ መንጋ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው- ግብርና ሚኒስቴር

126

ድሬዳዋ ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ)  የምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ተጎራባች ክልሎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ የተመራ ሉኡካን  ከድሬዳዋ አስተዳደር፣ ሐረሪና ሶማሌ ክልሎች ጋር በአንበጣ መከላከል ዙሪያ በድሬዳዋ ተወያይቷል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፤ በአካባቢው ዳግም የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የመስኖ ምርትና የእንስሳት ግጦሽን እንዳይጎዳ የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

መንጋው ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከልም በ13 አውሮፕላኖች የታገዘ የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ እስካሁን ከምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ጋር በመቀናጀት በ131ሺ ሄክታር መሬት ላይ የኬሚካል ርጭት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ ከ100 በላይ ተሸከርካሪዎች በርጭቱና መከላከሉ ሥራ መሰማራታቸውን አመልክተዋል፡፡

አንበጣው መንጋ እስካሁን ከግጦሽ መሬት በቀር በመስኖ ማሳዎች ላይ ያደረሰው  ጉዳት እንደሌለ የገለጹት ዶክተር ማንደፍሮ ፤ የተጀመረው የተቀናጀ የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ቀድሞ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ ሰብል ያወደመባቸው አርሶ አደሮች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል፡፡

እንደሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ መስሪያ ቤታቸው አንበጣን ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ አሰራር፣ አደረጃጀትና ዘመናዊ የኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖች አሟልቷል፡፡

በሀገሪቱ አስሩን ክልሎች በሶስት በመክፈል ሰንሰለቱን የጠበቀ አደረጃጀት መፈጠሩን የጠቆሙት ዶክተር ማንደፍሮ፤ የተፈጠረው አደረጃጀትም መረጃ በፍጥነት ወደ ማዕከል እንዲደርስ በማድረግ የመከላከሉ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ፣ውሃና ማዕድን ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በአስተዳደሩ ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት አለማድረሱን ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያ ጊዜ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ ጉዳት የደረሰባቸውን አርሶ አደሮች ለአንድ ዓመት በሴፍትኔት ከማቀፍ ሌላ  በምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶች ተደግፈው እንዲያገግሙ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ውይይት በሰብል ምርትና ምርታማነት ማደግ ላይ የተናበበ ዕቅድ ተዘርግቶ የተሻለ ሥራ ለመስራት ያመቻቸ መሆኑን  አቶ ኢብራሂም  ተናግረዋል፡፡

ከሶማሌ ላንድ የተነሳው የአንበጣ መንጋ ለሁለተኛ ጊዜ በምስራቅ የሀገሪቱ ተጎራባች ክልሎችን ጨምሮ በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች መታየቱም  ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም