ባለስልጣኑ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከገበያ ሰብስቦ ማስወገዱን ገለጸ

132

ደሴ/ጎንደር  ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ)  ለጤና ጠንቅ ሊሆኑ የሚችሉና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከገበያ ተሰብስበው መወገዳቸውን በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ሰሜን ምስራቅ ቅርንጫ አስታወቀ።

በጎንደር ከተማም በ695 የንግድ ሱቆች በተደረገ ፍተሻ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የተገመቱና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግም፣ መጠጥና የመዋቢያ እቃዎች ተሰብስበው ተወግደዋል።

በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ሰሜን ምስራቅ ቅርንጫ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጁሃር አበጋዝ እንደገለጹት በህብረተሰቡ ጤና ላይ ችግር የሚያደርሱ የተለያዩ የምግብ፤ መጠጥና መድሃኒት ዓይነቶች ገበያ ላይ አሉ።

ህብረተሰቡን ከዚህ ችግር ለመታደግ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ በምስራቅ አማራና አፋር ክልል በተደረገ ፍተሻ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ምርቶች እንዲወገዱና እንዲቃጠሉ መደረጉን ተናግረዋል።

“ምርቶቹ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው፤ የጥራት ችግር ያለባቸው፤ የትና መቼ እንደተመረቱ መግለጫ የሌላቸው፣ የጤና ችግር ከመፍጠራቸውም ባለፈ በአጭርና በረጅም ጊዜ እስከ ሞት ሊያደርሱ እንደሚችሉ የተረጋገጡ ናቸው” ብለዋል።

ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከፖሊስ፤ ከፍርድ ቤት፤ ከየዞኖቹ አስተዳደሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር በጅምላ አከፋፋዮችና ቸርቻሪ ሱቆች በተደረገ ክትትልና ቁጥር በመሆኑ ለነበረው ቅንጅት ምስጋና አቅርበዋል።

“86 ዓይነት ምርቶች መወገዳቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ የተለያዩ መድሃኒቶች፤ ደረቅ ምግቦች፤ ለስላሳ መጠጦች፤ የህጻናት ምግቦች፤ ዘይት፤ ጨው፤ ለውዝ ቅቤና ሌሎችም ይገኙበታል” ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ በበኩላቸው ከተያዘው ውስጥ ከአንድ ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች የተወገዱት ከዞናቸው ነው።

አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ከሰው ህይወት ይልቅ ጥቅማቸውን በማስቀደም ለመደበቅና የንግድ ተቋማቸውን ዘግተው ለመጥፋት ቢሞክሩም ተገቢ እንዳልሆነና በአዋጁ መሰረት በሰው ነፍስ ማጥፋት ወንጀል ሁሉ ሊከሰሱ እንደሚችሉ ማወቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ምርቶቹ ትላንት በኮምቦልቻ ከተማ ሲወገዱና ሲቃጠሉ በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፤ የደቡብ ወሎ ዞንና የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፤ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

በተመሰሳይም በጎንደር ከተማ ግምታቸው ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግብና መጠጦች መወገዳቸውን የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቋል።

በመምሪያው የኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አቶ አብልኝ ሙሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግብና መጠጦቹ የተያዙት በከተማው በሚገኙ 695 የንግድ ሱቆች ላይ በተካሄደ ክትትልና ቁጥጥር ነው፡፡

በንግድ ሱቆቹ በህገ-ወጥ መንገድ ለህብረተሰቡ ሲሸጡ ከተያዙት ምግብና መጠጦች መካከል ከ2ሺ በላይ እሽግ የለስላሳ መጠጦች፣ ከ500 በላይ የህጻናት የዱቄት ወተቶችና እሽግ የቆርቆሮ ምግቦች ይገኙበታል።

በተጨማሪም ለጤና ጎጂ መሆኑን የሚጠቁም አስገዳጅ ምልክት ያልተለጠፈባቸውና ገበያ ላይ እንዲሸጡ ያልተፈቀዱ 33ሺ ፓኬት የትንባሆ ምርቶችን ጨምሮ ደህንነታቸው ያልተረጋገጠና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የመዋቢያ ቅባቶችና ሻምፖዎችም እንዲወገዱ ከተደረጉት መካከል እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ለአንድ ሳምንት በተካሄደው ክትትል የመምሪያው ባለሙያዎችን ጨምሮ ከከተማው ጤና መምሪያና ከፖሊስ ተውጣጥቶ የተቋቋመ ግብረ-ሃይል መሳተፉን ገልጸው በድርጊቱ ከተገኙ የንግድ ድርጅቶች ባለቤቶች መካከል ሶስቱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በንግድ ህጉ መሰረት ክስ እንደተመሰረተባቸው ተናግረዋል።

ሌሎች 692 የንግድ ድርጅቶች ደግሞ ከዚህ ቀደም የፈጸሙት ህገ-ወጥ የንግድ ተግባር ባለመኖሩ በቃል ማስጠንቀቂያ የታለፉ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ህብረተሰቡ ማንኛውንም የታሸገ ምግብና መጠጥ እንዲሁም የመዋቢያ እቃና መድሃኒት ሲገዛ የመጠቀሚያ ጊዜውን በማየት ሊሆን እንደሚገባ ኃላፊዎቹ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም