11ኛው ከተማ አቀፍ የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ተጀመረ

119

ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ አስተዳደር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ከተማ አቀፍ የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ዛሬ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ አዘጋጅነት ተጀምሯል።

ከአዲሱ ክፍለከተማ ለሚኩራ በስተቀር አስሩም ክፍለከተሞች በሚሳተፉበት የባሕል ስፖርቶች ውድድር 500 የሚጠጉ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ፌስቲቫሉን የከፈቱት የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽነር በላይ ደጀን ገልፀዋል።

ለዘመናዊ ስፖርት መነሻ የሆነውን የባሕል ስፖርት ለማሳደግ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ያሉት አቶ በላይ የስፖርት ፖሊሲያችን ሁሉን ዓቀፍ እንደመሆኑ የባህል ስፖርቶችም እንደ ዘመናዊው ትኩረት እንዲያገኙ ይሰራል ብለዋል።

የባሕል ስፖርቶች በትምህርት ቤቶች ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን እንዲከናወኑ በማድረግ ተማሪዎች ባሕልና ትውፊታቸውን እንዲያውቁ የማድረግ ሥራ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ በአሥር ዓመት መሪ ዕቅዱም ለባህል ስፖርቱን ሰፊ ቦታ በመስጠት ትኩረት እንዲያገኝ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ኮሚሽነሩ 'ባሕላዊ ስፖርቶቻችን የአንድነታችንና የብዝሀነታችን መገለጫዎች እንደመሆናቸው መጠን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ልንጠቀምባቸው ይገባል' ብለዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፈቲያ መሀመድ የባሕል ስፖርቶች ክፍለ ከተሞች  የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉባቸው እንደሆኑ ገልፀው ውድድሩ ለመጪው የገና በዓል ድምቀት የሚሰጥ መሆኑን አክለዋል።

የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫሉ "የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የባሕል ስፖርት እንቅስቃሴ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን እንተጋለን!" በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ 'ራሳችንን ከወረርሽኙ በመጠበቅ መሆን አለበት' ብለዋል።

የገና፣ የገበጣ፣ የቀስት፣ የኩርቦ እንዲሁም የፈረስ ጉግስና ሽርጥ ጨዋታዎች የሚከወኑበት የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫሉ እስከ መጪው ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም ይቀጥላል።

ውድድሩን አሸንፈው የሚመረጡ ተጫዋቾች በአገር አቀፉ የባሕል ስፖርቶች ውድድር አዲስ አበባን ወክለው እንደሚሳተፉ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም