ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአራት ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ

1797

ደሴ ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮሮናን በመከላከል በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከአራት ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓቱ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ  እንደተናገሩት  ተማሪዎች የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፈው ለምርቃ መብቃት ችለዋል፡፡

በተለይ ኮሮናና ሀገራዊ የፀጥታ ችግሮች መሰናክል ቢፈጥሩም አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር በመጠቀም ትምህርታቸውን ተከታትለው እንዲመረቁ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታና ሳምንታዊ መረሃ ግብር  ትምህርታቸውን  የተከታተሉ  መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከልም 185 በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸውን  ዶክተር አፀደ ገልጸዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ቀይረው ሀገራችውንና ህዝባቸውን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአንድነትና የሠላም እሴት ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍም በእውቀት ላይ የተመሰረተ እገዛ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ከጽንፈኝነትና ሙሰኝነት ጸድተው ሀገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።

የዘንድሮ ተመራቂዎች ሀገር አፍራሹ የህወሓት ጁንታ በተወገደበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፤ ሀገር አፍራሶችን በጋራ መተጋል ውጤት እንደሚያመጣም በተግባር አሳይቶናል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ሁሉም በየተሰማራበት ጠንክሮ ከሰራ ያቀደውን ውጤት ማምጣቱ አይቀርም ያለቸው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው በሁለቱም ካምፓሶች ሦስት ነጥብ 98 አምጥታ ሁለት ዋንጫና ሌሎች ሽልማቶች ያገኘችው  ትግስት መኮንን ናት፡፡

”ምንም እንኳ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን ብናሳልፍም ለስኬት በቅተናል ያለችው ትግስት አስተማሪዎችና ቤተሰቦች ባደረጉላት እገዛ ለስኬት በመብቃቷ መደሰቷንም ገልጻለች፡፡

በተመረቀችበት የኢኮኖሚክስ ዘርፍም ህዝቧንና ሀገሯን በታማነት ለማገልግለ መዘጋጀቷን ተናግራለች፡፡

ሌላው በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቅ ሐጅ መሃመድ በበኩሉ ኮሮና ቫይረስና የህወሓት ጁንታ በትምህርታችን ላይ ጫና ቢያሳድሩም ተቋቁመን መመረቅ በመቻላችን ተደስተናል ብሏል፡፡

በተማረበት የሙያ ዘርፍ ህብረተሰቡን በታማኝነት ለማገልግ፣ የኢትዮጵያን አንድነትና ሠላም ለማስጠበቅም  የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡

ዩኒቨርስቲው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች አሰልጥኖ ያስመረቃቸውም ለ12ኛ ጊዜ እንደሆነ ተመልክቷል።