ለመተከል ዞን ተፈናቃዮች 50 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰብሰብ እንቅስቃሴ ተጀመረ

65

አሶሳ፣ ታህሳስ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም 50 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባበክር ከሊፋ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ በመተከል የጸጥታ ችግር ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ተፈናቃዮችን ለመደገፍ እና መልሶ ለማቋቋም ዕቅድ አዘጋጅቶ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካት በየደረጃው ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ጠቁመው፤ "በአሶሳና ካማሽ ዞኖች እንዲሁም ማኦኮሞ ልዩ ወረዳና አሶሳ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡን ማወያየት ተጀምሯል" ብለዋል፡፡

ባለሃብቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች የህብረተሰቡ ክፍሎች ድጋፉ ከሚሰበሰብባቸው መካከል እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡

የገቢ ማሰባሰብ እቅዱ በሚቀጥሉት 15 ቀናት ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ድጋፉ በዓይነት ጭምር እንደሚሰበሰብ አቶ ባበክር ገልጸው፤ በአጠቃላይ 50 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

ከአሶሳ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ የኔወርቅ ጥላሁን በሰጡት አስተያየት "በአገሪቱ አንድ አካባቢ የሚከሰት የነዋሪዎች መፈናቀል የሌላው ኢትዮጵያዊ ጉዳት ተደርጎ መወሰድ አለበት" ብለዋል፡፡

መንግስት ህግን የማስከበር ተቀዳሚ ሃላፊነት እንዳለበት የገለጹት ነዋሪዋ ለተጎጂ ወገኖች በሚደረግ ድጋፍ ግን ሰብዓዊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ መሳተፍ እንዳለበት አመልክተዋል።

"የነገ ሠላም ዋስትናችን ህዝብ ነው" ያሉት ወይዘሮ የኔወርቅ፤ ድጋፉን ከራሳቸው እንደሚጀምሩም ገልጸዋል፡፡

ለአገሪቱን ሠላም እና ልማት የማይፈልጉና ስልጣን በአቋራጭ መያዝ የሚፈልጉ ሃይሎች ለዞኑ ጸጥታ መደፍረስ ምክንያት እንደሆኑ የተናገሩት ደግሞ አቶ ኢብራሂም አዙቤር ናቸው፡፡

ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነም ተናግረዋል።

ወይዘሮ ብርሃኔ ሁሴን በበኩላቸው "ለመተከል ተፈናቃዮች አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ብናደርግ ደስ ይለኛል" ብለዋል፡፡

ከድጋፉ በተጓዳኝ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የግድ እንደሆነ ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዋ ወንጀለኞችን አጋልጠን በመስጠት የህግ የበላይት እንዲረጋገጥ መስራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም