የሠብዓዊ መብት ጥስት በሚያደርሱ አካላት ላይ አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል

103

አዲስ አበባ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በንጹሀን ላይ የሠብዓዊ መብት ጥስት እያደረሱ ባሉ አካላት ላይ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አመለከተ።

አካዳሚው ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በንጹሀን ላይ በተፈጸመው ጭፍጨፋ፣ መፈናቀልና የንብረት ጉዳት ላይ ያለውን አቋም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የአገርን ሠላምና ደህንነት የሚያውክ ወንጀልን በፅኑ እንደሚያወግዝም አስታውቋል፡፡

የአካዳሚው የቦርድ አባል ዶክተር ጸደቀ አባተ "በሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተዋለ ያለውን የሠብዓዊ መብቶች ጥሰትና እየደረሰ ያለውን የንብረት ውድመት ለማስቆም መንግስት በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል" ብለዋል።

በአገሪቷ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተስተዋለ ላለው የንጹሀን ግድያ፣  የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና የዜጎች መፈናቀል ተጠያቂ የሆኑ አካላትን በማጣራት ተገቢ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል።

መንግስት ሕዝቡን በማስተባበር በቀውስ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሠብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግና ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ሠላማዊ ሕይወት እንዲመሩ እንዲያደረግም እንዲሁ።

አስተማማኝ የፀጥታና የጥበቃ ዋስትና እንዲረጋገጥላቸውና የወደመባቸውን ንብረት ማግኘት በሚችሉበት ሁኔታ መስራት እንደሚገባም ነው የገለጸውት፡፡

በአገሪቷ የሕግ የበላይነትና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ የሳይንስ አካዳሚው እንደሚደግፍም ገልጿል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ የአገርን አንድነትና የሕግ የበላይነት ለማስከበር ላደረገው ተገድሎ አካዳሚው ክብር እንዳለውም ዶክተር ጸደቀ ተናግረዋል።

ዜጎች የሠላም እጦት አገርን ብሎም ሕዝብን ለመከራ ከመዳረግ በቀር ትርፍ እንደሌለው በመገንዘብ ልዩነታቸውንና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባሕል ማዳበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊነት በተላበሰና ከጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በፀዳ መልኩ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

አካዳሚው በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖችና ቤተሰቦቻቸው የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።

መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚወስደው እርምጃ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም