ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ከ571 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

71
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2010 ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ከ167 ሺህ ቶን በላይ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች ከ571 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ። አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን በ14 በመቶ በገቢ ደግሞ በ2 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተመልክቷል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ የባለስልጣኑን የሶስተኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 167 ሺህ 478 ቶን በመላክ ከ571 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል። በዕቅድ ከተያዘው አንጻር በመጠን 92 በመቶ፣ በገቢ ደግሞ 77 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው ገልጸዋል። 'ከሐምሌ ወር 2009 እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም ባሉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 159 ሺህ 652 ቶን ቡና፣ 6 ሺህ 461 ቶን ቅመማ ቅመምና 1 ሺህ 364 ቶን ሻይ ምርቶች በመላክ ከቡና 560 ሚሊዮን፣ ከቅመማ ቅመም 8 ሚሊዮንና ከሻይ 2 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል' ብለዋል። የዓለም ቡና ዋጋ መቀነስ፣ የላኪዎች በቅናሽ ዋጋ መሸጥና በወቅቱ አለመላክ፣ የገቢ መቀነስን ማካካሻ መጠን ጭማሪ አለመኖር፣ ትስስር አለመፈጠር፣ ሕገ ወጥ ንግድ ዝውውርን አለመግታትና ቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት ለቡና ወጪ ንግድ አፈጻጸም ማነስ ምክንያቶች እንደሆኑ ተጠቅሷል። በቅመማ ቅመም አፈፃጸም በኩልም በመጠን 53 በመቶ በገቢ ደግሞ 40 በመቶ ብቻ ማሳካት የተቻለ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 6 በመቶ፣ በገቢ ደግሞ 29 በመቶ መቀነሱ ተመልክቷል። ለቅመማ ቅመም ዘርፍ ግብይትና የጥራትና ጤና ምርምራ ማረጋገጫ ስርዓት አለመኖር፣ የዝንጅብል አቅርቦት አለመሻሻል፣ የድጋፍ ክትትልና ቁጥጥር ማነስ ለዕቅዱ አለመሳካት መንስኤዎች መሆናቸው ተገልጿል። ባለስልጣኑ የምርትና ምርታማነት መጨመር፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ጥራትና መጠን ለመጨመር፣ ህገ ወጥ ንግድና ዝውውርን በመከላከልና በመቆጣጠር ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውን አቶ ሳኒ አስታውሰዋል። በዘጠኝ ወራት የሕገ ወጥ ንግድና ዝውውር መስመሮችን ለይቶ ባከናወናቸው ተግባራት ከ 1 ሺህ 310 ቶን በላይ  ቡና በመያዝ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል። ሪፖርቱን ያደመጠው ቋሚ ኮሚቴው ባለስልጣኑ በቅመማ ቅመም የውጭ ግብይት፣ በታጠበ ቡና አፈጻጸም፤ በቡና ግብዓትና ጥራት፣ በመዳረሻ ማስፋፋት፣ በህገ ወጥ ንግድና ዝውውር ቁጥጥር ረገድ በስፋት እንዲሰራ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። አገሪቱ በዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ማሳደግ የሚያስችሉ ደንቦችን በፍጥነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት አጸድቆ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም አሳስቧል። በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ከ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን ዘርፉ ከግብርና ምርቶች የውጭ ግብይት 40 በመቶውን እንደሚሸፈን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ ቡናን ወደ 57 አገሮች፣ ሻይን ወደ ሶስት አገሮች እንዲሁም ቅመማ ቅመም ወደ 44 አገሮች ትልካለች። የቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የቡና ምርት በመላክ አምስተኛ ስትሆን በገቢ ደረጃ ግን ዘጠነኛና አስረኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ ከባለስልጣኑ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም