በገና በዓል ለ50 ሺህ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ድጋፍ ይደረጋል - የመዲናዋ የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ

51

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ለ50 ሺህ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ድጋፍ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጎፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍስሀ ጥበቡ ለኢዜአ እንዳሉት ለበዓሉ የሚደረገው ድጋፍ "አንድ ሰው ለአንድ ቤተሰብ" በሚል የተጀመረው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብርና የበጋ በጎ ፍቃድ ሥራዎች አካል ነው።

በዚህም በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ለአቅመ ደካሞች የሚደረገው ድጋፍ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባሕልን በማዳበር የሚገኘውን ደስታ ሙሉ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አቶ ፍስሃ ገልፀዋል።

ከሠብዓዊ ድጋፉ ባሻገር የገናን በዓልን ምክንያት በማድረግ 187 የአረጋዊያን መኖሪያ ቤቶችን የማደስ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ቤታቸው የታደሰላቸው የአገር ባለውለታ አረጋዊያን ጧሪና ደጋፊ በማጣት ቤታቸውን ማደስ ያልቻሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በገና ስጦታ የሚበረከትላቸው ሠብዓዊ ድጋፍም በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አስተባባሪነት ለሚደረገው ሠብዓዊ ድጋፍ የከተማዋ ነዋሪዎችና የንግዱ ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንም አክለዋል።

በአይነት የሚደረገው ድጋፍ ለበዓል የሚሆኑ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ እንደሚያካትት ጠቁመዋል።

ለአረጋዊያኑና ለአቅመ ደካሞቹ ከእርድ እንስሳት ውጭ የሚደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆንም ምክትል የቢሮ ሃላፊው አስታውቀዋል።

ቢሮው 50 ሺህ ለሚሆኑ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች የእንኳን አደረሳችሁ የገና በዓል ስጦታ ለማበርከት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አቶ ፍስሃ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም