በኦሮሞ ህዝብ ስም በኦነግ ሸኔ የሚፈጸም ማንኛውንም ህገ ወጥ እንቅስቃሴ አንታገስም - የሊበን ወረዳ ነዋሪዎች

57

ነገሌ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ ) በኦሮሞ ህዝብ ስም በኦነግ ሸኔ የሚፈጸም ማንኛውንም ህገ ወጥ እንቅስቃሴ እንደማይታገሱ የጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ ትናንት በየአካባቢያቸው ከቀበሌ መስተዳድሮች፣ ከፖሊስና ከፍትህ አካላት ጋር በሰላም ጉዳይ መክረዋል፡፡ 


የህግ የበላይነት እንዲከበር የዞኑ ህዝብ ባደረገው ትብብር አብዛኛዎቹ የኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድን አባላት ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡

 በዞኑ የሊበን ወረዳ ነዋሪ አቶ ሲዶ ኦዳ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት በአካባቢያቸው ከ10 የማያንሱ ግለሰቦች ኦነግ ሸኔን አትደግፉም በሚል ታፍነው በመወሰዳቸው የደረሱበት አይታወቅም።

"የኦሮሞን ህዝብ ነጻ አወጣለሁ የሚለው የጥፋት ቡድኑ በአካባቢያችን ተረጋገተን በሰላም እንዳንኖር እረፍት እያሳጣን በመሆኑ ከአሁን በኋላ  አንታገሰውም" ብለዋል፡፡


"ኦነግ ሸኔ ከህወሐት ጁንታ የጥፋት ቡድን ተልእኮ በመቀበል ሀገር ለማፍረስ የኦሮሞን ህዝብ በማፈንና በማሰቃየት ያደረሰውን በደል ቤት ይቁጠረው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

"በኦነግ ሸኔ በብሄር ብሄረሰቦች ላይ  የሚፈጸም ጥቃት የኦሮሞን ህዝብ መልካም ገጽታ እያበላሸ ነው" ያሉት ደግሞ  ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ ቱኬ ኡዴሳ ናቸው።

የህግ የበላይነት ተከብሮ ዘላቂ ሰላም እስኪመጣ የጥፋት ቡድኑን አባላት ከማጋለጥና ለህግ አሳልፎ ከመስጠት እንደማይቆጠቡ ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ኅላፊ ምክትል ኮማንደር በቃሉ በለጠ የጥፋት ቡድኑ አባላት ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ የዞኑ ህዝብ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

"በግንዛቤ ጉድለት በመታለል የኦነግ ሸኔ የጥፋት ተልእኮ አስፈጻሚ የነበሩ ከ400 በላይ ወጣቶች በአባቶች ምክርና ተግሳጽ ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሰዋል" ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ በመከባበርና በመቻቻል የሚያምን አቃፊና ይቅር ባይ በመሆኑ ቀሪ የቡድኑን አባላት መክሮ መመለስ አስፈላጊ መሆኑን አመልከተዋል።

ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑትን ለፖሊስ በመጠቆም  ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጥፋት ቡድኑን ተልእኮ በመቀበል ሲንቀሳቀሱ ከነበሩና ወደ ሰላማዊ ህይወት ከተመለሱ መካከል 52 ሴቶችና 353 ወንዶች የህግ የበላይነትና የስነ ልቦና ስልጠና መውሰዳቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም