ከምናባዛው ምርጥ ዘር ሽያጭ በዓመት ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኘን ነው-የሰሜን ሸዋ አርሶ አደሮች

55

ፍቼ፣ ታህሳስ 23/2013/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከምርት ሽያጭ በዓመት ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገለጹ። 

በዞኑ ሰባት ወረዳዎች 7 ሺህ 600 አርሶ አደሮች በምርጥ ዘር ብዜት ስራ መሰማራታቸውን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ 

በዞኑ በምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ አርሶ አደሮች የሚያባዙትን የስንዴ፣ የሽንብራና የገብስ ምርጥ ዘር ለህብረት ስራ ማህበራት በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ኑሯቸውን እያሻሻሉ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዞኑ  የሂደቡ አቦቴ የኑኑ ጀቤ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉጌታ ማሞ እንደገለጹት ባለፈው አመት በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ካባዙት የሽንበራ ምርጥ ዘር ያገኙትን 40 ኩንታል ምርት በመሸጥ ከ104 ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል ።

ዘንድሮም በመኽር ወቅት ያባዙትን  40 ኩንታል የሽንብራ ዘር ለማህበራቸው በማቅረብ ኩንታሉን 2ሺህ 600 ብር ሂሳብ በመሸጥ ተመሳሳይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

"ገቢዬ እየተሻሻለ በመምጣቱ  ለአካባቢው አገልግሎት የሚሰጥ የገጠር ወፍጮ ለማቋቋምና ልጄን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየከፈልኩ ለማስተማር በቅቻለሁ" ብለዋል።

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ጀንበሩ ሙሃባ ካለፈው ሶስት ዓመት ጀምሮ ከመደበኛ እርሻ በተጓዳኝ ለቢራ ብቅል በሚሆን ገብስ  ብዜት መሰማራታቸውን አመልከተዋል።

ምርታቸውን ለፋብሪካዎች በማቅረብ አንዱን ኩንታል እስከ 2 ሺህ 900 ብር እየሸጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዓመት እስከ 35 ኩንታል ምርት አምርተው ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከምርት ሽያጭ እስከ 101 ሺህ ብርና ከዛ በላይ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ 

ሌሎች አርሶ አደሮችም ከእርሳቸው ልምድ በመቅሰም በዘር ብዜት ስራ እየተሰማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ ግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸው ምክርና እገዛ ለገቢያቸው ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቁመው አስተዳደሩም ገበያ በማፈላለግ ምርታቸውን በጥሩ ዋጋ እንዲሸጡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ 

"በመኽር ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ካባዛሁት የስንዴ ምርጥ ዘር ሽያጭ 78 ሺህ ብር አግኝቻለሁ "ያሉት ደግሞ የግራር ጃርሶ ወረዳ የወርጡ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰርቤሳ ገመዳ ናቸው።

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የአግሮኖሚና የአዝርዕት ልማት ቡድን መሪ አቶ በላይ ደረጄ በዞኑ ሰባት ወረዳዎች  7 ሺህ 600 አርሶ አደሮች በምርጥ ዘር ብዜት ስራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ ባለፈው አመትና ዘንድሮ በ2ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 58 ሺህ ኩንታል የስንዴ፣ የሽንብራና የገብስ ምርጥ ዘር አምርተው በመሸጣቸው  እውቅና የተሰጣቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ከምርምር ተቋማት ጋር አብሮ በመስራት እውቅና ያገኙት በዞኑ የሂደቡ አቦቴ፣ የግራር ጃርሶ፣ ጅዳ፣ ደገም፣ ኩዩ፣ ያያ ጉለሌና ውጫሌ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች መሆናቸውን ባለሙያው አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም