የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ሰራተኞች ድርጅቱ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ችግኝ ተከሉ

132
አዲስ አበባ ሀምሌ 14/2010 በየዓመቱ ችግኝ የሚተክሉ ተቋማት ችግኝ ከመትከል በላፈ መንከባከብ እንዳለባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የአንበሳ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ድርጅት ሰራተኞች ገለጹ። የድርጅቱ ሰራተኞች ተቋሙ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት አስመልክቶ ዛሬ በኦሮሚያ ልዩ ዞን አቃቂ ወረዳ እንስላሌ ቀበሌ ከ300 በላይ ችግኞችን ተክለዋል። የአንበሳ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ድርጅት የሰው ሃይል አስተዳደር ባለሙያ አቶ ዘሪሁን ገብረሚካኤል የመንግስት ተቋማት በየዓመቱ ችግኝ ቢተክሉም የመንከባከብ ስራው ትኩረት እንደማይሰጠው ይገልጻሉ። ይህም የሚመነጨው ተቋማት በተደራጀ መልኩ ክትትል አለማድረግና ችግኙ ከሚተከልበት አካባቢ የሚገኙ አካላት ጋር ያለው የቅንጅት አሰራር ጠንካራ ባለመሆኑን ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል። የመንግስት ተቋማቱ የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራ የስራ ክፍል በማቋቋምና በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ በመቅጠር በዘላቂነት የችግኝ መትከሉ ስራ ውጤታማ እንዲሆን መሰራት አለበት ብለዋል። ችግኞቹ ጸድቀው ለፍሬ እንዲበቁ ተቋማት የአካባቢ ጥበቃን የእቅዳቸው አንድ አካል ማድረግ እንደሚገባ ነው አቶ ዘሪሁን ያስረዱት። የድርጅቱ የውስጥ ኦዲተር ወይዘሮ የአይኔአበባ በላይነህ በበኩላቸው የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከመንግስት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዓመታዊ እቅድ በማውጣት የችግኝ ተከላ ስራ ላይ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል ገልጸዋል። የመንግስት ተቋማቱ ችግኝ የሚተክሉ ሰራተኞች ችግኙን በየጊዜው ለመንከባከብ ጊዜ ስለማይኖራቸው ችግኙን በባለቤትነት ወስደው የሚንከባከቡ ባለሙያዎችን ቀጥሮ ማሰራት ሌላኛው መፍትሔ ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል። የአንበሳ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ድርጅት የአውቶቢስ ትኬት ቆራጭ አቶ ዘሪሁን ሞላ በአገር አቀፍ ደረጃ ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ስራ የዘመቻ እንጂ ወጥነትና ዘላቂነት ያለው እንደሌለው ተናግረዋል። ለዚህም ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው የመንግስት ተቋማት፣የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችና ችግኙ የሚተከልብት ቦታ ያሉ አመራሮች ተናበው መስራት የሚያስችላቸውን አሰራር መዘርጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ችግኝ ተክሎ እስከሚጸድቅ መንከባከብ የየተቋማቱ የእቅድ አካል ከሆነ ሰራተኛው ችግኙን ያለበት ቦታ ድረስ ሄዶ መንከባከብ ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል። የአንበሳ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ድርጅት ስራ እስኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ በበኩላቸው በድርጅቱ ችግኝ የመትከልና በአጠቃላይ በአካባቢ ጥበቃ የሚሰሩ ስራዎች የማህበራዊ አገልግሎት እቅድ አካል ነው። በተቋማቸው መልካም ተሞክሮ ቢኖርም ችግኞች ጸድቀው ፍሬ እስኪያፈሩ በዘላቂነት የመከታተል ተግባር እምብዛም ውጤታማ አይደለም ብለዋል። በቀጣይም የችግኝ ተከላው ስራ ልፋትና ተተከለ ለማለት ብቻ እንዳይሆን እስኪጸድቅ ድረስ ድርጅቱ አስፈላጊውን እንክብካቤና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የአንበሳ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ድርጅት ከተመሰረተበት ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ ለህብረተሰቡ የትራስፖርት አግልግሎት በመስጠት ፈርቀዳጅ የሚበል የትራንስፖርት ተቋም ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም