ለአካባቢያቸው ሠላም መጠናከር እንደሚሰሩ በድሬዳዋ የሚገኙ የኃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ

62

ድሬዳዋ፣ ታህሳስ 23/2013(ኢዜአ) ለአካባቢያቸው ሠላምና የህዝብ አብሮነት መጠናከር አበክረው እንደሚሰሩ በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ የኃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም ፣ አብሮነት፣ ኃይማኖትና ብዝሃነት ዙሪያ በድሬዳዋ ከተማ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ትናንት ተጠናቋል፡፡

በወቅቱ ኢዜአ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊ የኃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች እንደተናገሩት፤ በድሬዳዋ በመተባበርና አንድነት አብሮ የመኖር የዘመናት እሴቶች ለማስቀጠል ጠንክረው ይሰራሉ፡፡

የድሬዳዋ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ-ትጉሃን ቀለመወርቅ ቢምረው በሰጡት አስተያየት በአብሮነት የአካባቢያቸውን ሠላም በመጠበቅ ሀገራዊ ለውጡን ለማጎልበት አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው ሠላምና አብሮነት ለመሸርሸር የሚሞክሩ አካላትን በማጋለጥ የድሬዳዋን ኀብረተሰብ መልካም እሴቶችን ተጠብቆ እንዲዘልቅ መደላድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምድ እንዲጎለብት ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ሼህ አሊያስ አልይ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኃይማኖትና ብሔር ሽፋን የአካባቢውን ሠላምና ልማት ለማደናቀፍ ሲሰሩ የነበሩትን የጥፋት ሃይሎች በመተባበር በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በድሬዳዋ የተሻለ ሠላም መስፈኑን አስረድተዋል፡፡

ሠላማችንን አስተማማኝ ለማድረግ የኃይማኖት አባቶች ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በትጋት በመስራት ሁሉም ለሀገሩ ልማትና አንድነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንሰራለን ብለዋል፡፡

ሠላም ከራስና ከቤተሰብ ይጀምራል ያሉት ደግሞ የሀገር ሽማግሌው አቶ ሐሰን አሊ ናቸው፡፡

አቶ ሐሰን እንዳሉት፤ የሁሉም ነገር መሠረቱ ሰላም በመሆኑ በውይይቱ ያገኙትን ግንዛቤ ለአካባቢው ማህበረሰብ በማካፈል ነዋሪው ለሠላሙና ልማቱ የድርሻቸውን እንዲወጣ አበክረው ለመስራት ተዘጋጅተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የክልል ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ መጋቢ ይታገሱ ኃይለሚካኤል ተሳታፊዎቹ ከውይይቱ ያገኙትን ግንዛቤ በመላው ድሬዳዋ በማዳረስ አስተማማኝ ሠላምና አንድነት እንዲሰፍን መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዜጎች ለሠላምና አንድነት መጠናከር ያላቸውን የማይተካ ሚና የሚያስገነዝቡ መሰል ውይይቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚያካሂዱም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም