በሀዋሳ ከተማ ለትምህርት ቤቶችና ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ከተማ ለትምህርት ቤቶችና ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደረገ
ሐዋሳ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) በሐዋሳ ከተማ ለሚገኙ ሶስት ትምህርት ቤቶችና አቅመ ደካሞች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቁሳቁስና ምግብ ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፉን ያደረገው ኤስ ኦ ኤስ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ለአላሙራና ቡሽሎ የመጀመሪያና ለሎቄ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ እንዲሁም ለ1ሺህ 200 አቅመ ደካሞች የምግብ ድጋፍ አድርጓል።
የኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ፕሮግራም ሐዋሳ ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ ደጀኔ ትላንት በተካሄደ ስነ ስርአት ድጋፉን አስረክበዋል ።
ለቤተ ሙከራ፣ ለቤተ መጻህፍትና ለመማሪያ ክፍሎች የሚሆኑ ኬሚካሎች፣ መደርደሪያና መቀመጫዎች፣ ማጣቀሻ መጽሀፍት ጨምሮ የስፖርት ትጥቅ፣ የህጻናት መጫወቻዎች፣ የንጽህና መጠበቂያዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች ለትምህርት ቤቶቹ በድጋፍ ተበርክተዋል ።
በተመሳሳይ ለ1 ሺህ 200 አቅመ ደካሞች የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ዘይትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
ለትምህርት ቤቶቹና ለአቅመ ዳካሞች የተደረገው ድጋፍ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገበት መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኅላፊ አቶ ታሪኩ ዱካሞ ድርጅቱ የትምህርት ዘርፉን ለማጠናከር እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
"ድጋፉ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት እየተከናወነ ያለውን ተግባር ያግዛል" ያሉት ደግሞ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ሐላፊ አቶ ደስታ ዳንኤል ናቸው።
የቡሽሎ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ሀረገወይን ገነነ "የተደረገው ድጋፍ በትምህርት ቤቱ የተሟላ ትምህርት ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል" ብለዋል።
"ድርጅቱ እያደረገልኝ ያለው ድጋፍ ልጆቼ ከትምህርታቸው ሳይስተጓጎሉ እንዲማሩ አስችሏቸዋል" ያሉት ደግሞ በከተማው የቱሎ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መሣይ ጌታቸው ናቸው።