የወያኔ ባለስልጣናት ለዳኞች ስልክ እየደወሉ እንዲህ አይነት ፍርድ ስጡ የሚሉበት የፍትህ ስርዓት ተፈጥሮ ነበር - አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

171

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የወያኔ ባለስልጣናት ለዳኞች ስልክ እየደወሉ እንዲህ አይነት ፍርድ ስጡ የሚሉበት የፍትህ ስርዓት ተፈጥሮ ነበር” ሲሉ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ገለጹ።\

በወቅታዊ የአገራዊ ሁኔታ እና በቅርቡ ባሳተሙት ‘የታፋኙ ማስታወሻ’ መጽሐፋቸው ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደገለጹት፤ የህወሃት ቡድን የፍትህ ስርዓቱን አበላሽቶት ቆይቷል።

በፍርድ ቤት የሚቀርቡ ክሶችና ውሳኔዎች በሙሉ በህወሃት ቡድን የተደራጀ መረጃ የተመሰረቱ እንደነበሩ ገልጸዋል።

“የወያኔ ባለስልጣናትም ለዳኞች ስልክ እየደወሉ እንዲህ አይነት ፍርድ ፍረዱ ብለው ትዕዛዝ በሚሰጡበት ሁኔታ የሚሰራ የፍትህ ስርዓት እንደነበረ ነው የማውቀው” ብለዋል።

“በአፋኝነት ብቻ አይደለም የወያኔ እስረኛ ነኝ ያልኩት” ሲሉ የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው፤ እስር ቤትን ብቻ ሳይሆን የፍትህ ስርዓቱን በሙሉ ይቆጣጠሩ የነበሩት የህወሃት ሰዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ከህወሃት ሰዎች ጋር የመስራት ልምድ እንደነበራቸው ያስታወሱት አቶ አንዳርጋቸው፤ በሂደት መገንዘብ እንደቻሉት የፍትህ ተቋማት፣ ደህንነትና መከላከያ ሰራዊት በጠቅላላ የህወሃት ቡድን ተቆጣጥሮት እንደነበር ተናግረዋል።

“ተቋማት በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ነበር” በማለት ገልጸው፤ የግለሰብና የቡድን ህይወት ጭምር በህወሃት ሰዎች ቁጥጥር ስር ወድቆ እንደነበር ገልጸዋል።

“በእኔ ላይ የደረሰ አፈና በአገር ላይ ጭምር የደረሰ አፈና ነበር” በማለት የቡድኑን የአፋኝነት ጥግ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም