አለም ወረርሽኞችን ለመቋቋም አሁንም ሙሉ በሙሉ አልተዘጋጀም''- የአለም ጤና ድርጅት

99

'የአለምን ህዝብ የከፋ ጉዳት ላይ የጣሉ ወረርሽኞችን ለመቋቋም ''አለም አሁንም ሙሉ በሙሉ አልተዘጋጀም'' ሲል የአለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

ከተከሰተ አንድ አመት ያስቆጠረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፤ማህበራዊ እና ሌሎች ቀውሶችን እያስከተለ ይገኛል።

መንግስታት ለሚከሰቱ ድንገተኛ ወረርሺኞች የሚሰጡት ምላሽ አጥጋቢ መሆን እንዳለበትም የአለም ጤና ድርጅት ጠቁሟል።

የአለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋዎች ሥራ አስፈፃሚ ዶ / ር ማይክል ሪያን በሰጡት መግለጫ''አለም ከዚህ የከፋ ወረርሽኝ ሊያጋጥማት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ወረርሺኞችን ተባብሮ መከላከል ላይ አለም ጠንክሮ እንዲሰራ ያሳሰቡት ዶ/ር ማይክ ወደፊት ሊከሰት የሚችለው የከፋ ወረርሺኝ ይቅርና አሁን ያለውን ለመቋቋም አለም “ሙሉ በሙሉ” ዝግጁ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት አዲሱ የፈረንጆች አመት ከመግባቱ በፊት የመጨረሻውን የአመቱ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው ይህ የተባለው።

የኮሮና ቫይረስ በአለም ዙሪያ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ገልፀው፤ ቅድመ መከላከሉ ላይ ተገቢው እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት አለም በባህሪ ሳይንስ ፣በክትባት፣ በተፈጥሮ እና ማህበራዊ በሳይንስ ፣በምርምር እና በሌሎች ዘርፎች በተሻለ ስፍራ ላይ ብትገኝም ከዚህም ለከፋ ችግር መዘጋጀት እንደሚገባ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

እንደ ጆህን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዛዊ መረጃዎች ከሆነ በአለም ዙሪያ ከ81 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በቫይረሱ ሲጠቁ፤የሟቾች ቁጥር ደግሞ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

ተስፋ ሰጪ ውጤት ያሳዩ ክትባቶች የተገኙ ቢሆንም ለሁሉም የማድረስ አቅም አለመፈጠሩን ድርጅቱ ማስታወቁ ይታወሳል።

የአለም ጤና ድርጅት አማካሪ የሆኑት ዶ / ር ብሩስ አይልዋርድ “ይህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ዝግጁ አለመሆናችንን እየነገረን ነው '' ሲሉ ተናግረዋል።

ወረርሺኙ እጅግ እየተሰራጨ መጥቶ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ማዕበል ውስጥ አለምን እያስገባ መሆኑን አማካሪው ገልጸዋል።

ምንጭ-አናዶሉ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም