በዶሃ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

77

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20/2013 (ኢዜአ) በኳታር መዲና ዶሃ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአገሪቷ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሀብት ማሰባሰብ ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጿል።

የሀብት ማሰባሰብ ስራው በዋናነት በሕግ ማስከበር ሂደቱ የተሰደዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም፣ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረተ ልማቶችን ለመጠገንና ዜጎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ለማገዝ ያለመ መሆኑንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ማህበርን ጨምሮ ስድስት ሕዝባዊ ማህበራት፣ሁለት የሃይማኖት ተቋማት፣የኤምባሲ ሰራተኞችና እንዲሁም በዶሃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ወደ አገር ቤት መላኩን ኤምባሲው አመልክቷል።

በድጋፍ ማሰባሰብ ሂደቱ ከ400 በላይ ዜጎች ተሳታፊ መሆናቸውንም ነው ኢምባሲው ያስታወቀው።

መንግስት በትግራይ ክልል ሲያካሄድ የነበረውን የሕግ ማስከበር እርምጃ አጠናቆ ወደ "ወንጀለኞችን ማደንና መልሶ ማቋቋም" ምዕራፍ መሸጋገሩ ይታወሳል።

በክልሉ በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አማካኝነትም በትግራይ ክልል የሚገኙ ህዝባዊ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም