በትግራይ በማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የላቀ እድገት ለማምጣት በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ

127
መቀሌ ሀምሌ 14/2010 በትግራይ ክልል በማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የላቀ እድገት እንዲመጣ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን፣ ዳያስፖራዎችና መላው የክልሉ ህዝብ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ። በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ምሁራንና ዳያስፖራዎች በመቀሌ ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው ዓለም አቀፍ የምሁራን ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው እንዳሉት፣ የአንድ አገር ወይም ክልል እድገት የሚወሰነው በህዝቡ የነቃ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ነው። ምሁራንና ዳያስፖራዎቹ እንዳሉት የክልሉን እምቅ የኢንዱስትሪ ጥሬ ሃብቶች ወደ ላቀ የህዝቡ ተጠቃሚነት ለማሸጋገር በቅንጅት መስራት ወሳኝ ነው። በኮንፈረንሱ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን መካከል የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብራህቱ መለስ እንዳሉት፣ በክልሉ የሚገኙ የኢዱስትሪ እምቅ ጥሬ ሃብቶችን ወደ ልማት ለመቀየር የሚያስችል ሃብትን የማሰባሰብ ስራ በስፋት መስራት ያስፈልጋል። በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ የሚመደቡትን ወደ ልማት ለመቀየር ክልሉ በአምስት የልማት ኮሪደሮች እንዲከፋፈል በማድረግ ዝርዝር ጥናት ማካሄዱንም ሚኒስትር ዲኤታው አመልክተዋል። ሥራውን ከግብ ለማድረስ የሃብት ማሰባሰብ ሥራ በስፋት ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር መብራህቱ "ለእዚህም ከግል ባለሃብቶችና የፋይናንስ ተቋማት ጋር የልማት ትስስር አጋርነት መፍጠር ወሳኝ ነው" ብለዋል። ከሁሉም በላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ መላው የክልሉ ህዝብና ምሁራን በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ዶክተር መብራህቱ አስገንዝበዋል። የክልሉ ተወላጅ ዶክተር ሙሉ ገብረኢየሱስ  በበኩላቸው ለኢንዱስትሪ እድገት ብቁ የአመራር ክህሎትና ቁርጠኝነት፣ የተረጋጋ ሰላም፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ልዩ የማበረታቻ ድጋፎችን መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። "በተለይ ለለውጥና ለልማት ክፍት የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር፣ የፋይናንስ ድጋፍና ያልተማከለ የአመራር ሂደትን መከተል ወሳኝ ናቸው" ያሉት ዶክተር ሙሉ እነዚህን ግቦች ለማሳካት የምሁራን ሚና የላቀ መሆኑን አስረድተዋል። መኖሪያቸውን ለረዥም ዓመታት በጀርመን አገር ያደረጉ ዳያስፖራ ዶክተር መሀመድ እንድሪስ በበኩላቸው አገሪቱን በተለይ ደግሞ ትግራይን በልማት ለማሳደግ ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነው በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። "የማኑፋክቸሪንግም ሆነ ሌሎች የልማት ዘርፎች የሚሳኩት ህዝቡን፣ ምሁራንና ባለደርሻ አካላትን በንቃት በማሳተፍና ተጠቃሚ በማድረግ ነው" ያሉት ደግሞ የቀድሞ የመቴክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘ ናቸው። ሜጀር ጀነራል ክንፈ በኮንፈረንሱ ላይ በትግራይ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪና የማዕድን ሃብት ላይ ትኩረት አድርገው ጥናታዊ ጽሑፍ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ትላልቅ ባለሃብቶችና መንግስት በሚፈጥሩት ልማት ብቻ ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ  አይቻልም። ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከተፈለገ መላውን ህዝብ ማሳተፍና የአግሮ ፕሮሰሲንግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ማጠናከር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን አመልክተዋል። የመንግስት ዋንኛ ሚና ህዝቡን ወደ ልማት መምራት መሆኑን ጠቁመው ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ለማሳደግ ለሁሉም የልማት እድገቶች መሰረት ለሆነው የግብርናው ዘርፍ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል። የሚፈለገውም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እድገት ለማረጋገጥም መላው የክልሉ ህዝብ፣ ምሁራንና ባለሃብቶች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል። ከ1 ሺህ 300 በላይ ምሁራን፣ ዳያስፖራዎችና ሌሎች ከክልሉ የተለያዩ መንግስታዊ አካላት እየተሳተፉበት ያለው ዓለም አቀፍ የምሁራን ኮንፈረንስ ነገ ከሰዓት በኃላ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም