በሀገሪቱ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለመደገፍ ከ8.6 ቢሊዮን ብር በላይ ተመደበ

107

ጋምቤላ ታህሳስ 19/2013(ኢዜአ) በሀገሪቱ የኢንዱሰትሪውን ዘርፍ በመደገፍ ለማጠናከር ከስምንት ቢሊዮን 600 ሚሊየን ብር በላይ ተመደቦ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል አነስተኛና መከከለኛ ማኖፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ልማት ማስፋፈያ ባለስጣልን ገለጸ።

የፌዴራልና ክልል ባለድርሻ አካላት ዘርፉ በሚሰፋበትና በሚጠናከርበት ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሄደዋል።

የባለስጣኑ ምክትል ዳሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ወልደማሪያም በውይይት መድረኩ እንዳሉት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪውን በማስፋትና በማጠናከር የኢኮኖሚው መሪነቱን እንዲይዝ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል።

በጋምቤላ ክልል ዓሳን ጨምሮ ለኢንዱስተሪ ልማት የሚውል ሰፊ የእንስሳት፣ማዕድንና ሌሎች የተፈጥሮ  ሀብቶች ቢኖሩም በዘርፉ የተከናወኑት ስራዎች ውስን መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ዘርፉን በማጠናከር እንደ ሀገር ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚውን እንዲማራ ለማገዝ  መዋቅራዊ ችግሩን ለመፍታት ሁሉም በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

እንደ ሀገር ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለመደገፍ አስፈላጊው በጀት ተመድቦ ሲሰራ መቆየቱን  ጠቁመው በተያዘው የበጀት ዓመትም ከስምንት ቢሊዮን 600 ሚሊየን ብር በላይ ተመድቦ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

የበጀቱ ድጋፍ ከሚደረግላቸው መካከል በ1ሺህ 999  አነስተኛና መከከለኛ   ኢንዱስትሪዎችና ማንፋክቸሪንግ የተደራጁ አካላት በብድር የሚሰጣቸው እንደሚገኝበት አስረድተዋል።

በዚህም ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

በዘርፍ የተሻለ አፈፃፀም ከተመዘገበ በቀጣይም ዘርፉን ለማጠናከር የተሻለ በጀት ሊመደብ እንደሚችል ምክትል ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው  የኢንዱስትሪው  ልማት ዘርፍ እንደ ሀገር በመልካም ሂደት ላይ የሚገኝ ቢሆንም በክልሉ ሰፊ ክፍቶትች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ዘርፉ ለመዋቅራዊ ሽግግሩ ዓይነተኛ መሳሪያ በመሆኑ  በቀጣይ የተጠናከሩ ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

በተለይም ካሁን በፊት በክልሉ ከኢንዱስትሪ ልማቱ ጋር ተያይዞ በልማት ባንክ በኩል የነበረው የብድር ሄደት ብልሹ አሰራሮች እንደነበሩበት አስታውሰው በቀጣይ ችግሮች  እንዳይደገሙ  ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል  ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ጌታቻው ዋቂ እንደተናገሩት በክልሉ ካሁን በፊት ከብድር ጋር የተያያዙ ብልሹ አሰራሮች እንዳይደገሙ ባንክ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ባንክ በተለይም የአካባቢውን ማህበረሰብን በሚያበረታታ መልኩ የብድር አግልግሎት ለመስጠትም ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

በጋምቤላ ከተማ ለግማሽ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ የኢትየጵያ ግብዓት  አቅርቦት፣ ኢትዮ- ኢንጅነሪንግ፣ ልማት ባንከ ፣የክልሉ  ካቢኔ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም