በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በባለሀብቶች ለሚከናወኑ ተግባራት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል...ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

88

ሀዋሳ፤ታህሳስ 18/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በባለሀብቶች ለሚከናወኑ ተግባራት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል አስታወቁ።

በሀዋሳ ከተማ በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጭ ለሚገነባ የዘይት ማምረቻ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት ለበርካታ ዓመት በአምራች ኢንዱስትሪው መስክ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር ውስን ነበር።

ከለውጡ ወዲህ ግን መንግስት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ባከናወናቸው ተግባራት በርካታ ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራት ፍቃድ ወስደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶች በስፋት የሚገኙበት በመሆኑ በሀገሪቱ አሁን በተፈጠረው መልካም ሁኔታ ቀድሞ የኢንዱስትሪ ማዕከል መሆን እንደቻለ ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ በወር ከ48 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለዘይት ግዥ እንደምታወጣ ተናግረው"ይህም ሆኖ በወር ከሚያስፈልገው 57 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ውስጥ ከውጭ ማስመጣት የተቻለው 40 ሚሊዮን ሊትር ብቻ ነው" ብለዋል።

በሀገር ውስጥ ያሉ የዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቱት ዘይት ካለው ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር 12 በመቶ ብቻ የሚሸፍን መሆኑን ጠቁመዋል።

የሀገር ውስጥ አምራቾች በመስኩ እንዲሰማሩ ማበረታታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሀዋሳ ከተማ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተጣለት የዘይት ማምረቻ ኢንዱስትሪ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊው ደጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በባለሀብቶች ለሚከናወኑ ተግባራት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ሀገሪቱ የምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫ የግል ባለሀብቶችን የሚያበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል መንግስትና ህዝብ ባለሀብቶችን በመቀበልና በተገቢው መንገድ በመደገፍ አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ያለው ሰላምና ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በተለያዩ መስኮች ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ለማበረታታትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

"ከተማው ቀደም ሲል ከነበረው ችግር በመላቀቅ ሰላማዊ ሁኔታ የሰፈነበት በመሆኑ በባለሀብቶች ተፈላጊነቱ እየጨመረ ነው" ያሉት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መስኮች ለመሰማራት ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የዘይት ማምረቻ ኢንደስትሪው በተቀመጠለት ጊዜ ግንባታው አጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የአማ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት አቶ አንድነት ጌታቸው እንዳሉት ለግንባታ በተረከቡት 100 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው የምግብ ዘይት ማምረቻ ኢንዱስትሪ በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል።

ኢንዱስትሪው ወደ ስራ ሲገባ በመጀመሪያ ዙር በዓመት 22 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንደሚያመርት ተናግረዋል።

ተጨማሪ ማሽኖችን በመትከል ከሶስት ዓመታት በኋላ ምርቱን ወደ 68 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሊትር ለማሳደግ እቅድ መያዙን አመላክተዋል።

ፋብሪካው ማምረት ሲጀምር ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ባለሀብቱ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም