የከተሞች ምግብ ዋስትና መርሃ-ግብር ተጠቃሚዎች የዘላቂ ኑሮ ዋስትና ስልጠና በዚህ ወር ይጀምራል

214
አዲስ አበባ ሀምሌ 14/2010 የመጀመሪያው ዙር የከተሞች ምግብ ዋስትና መርሃ-ግብር ተጠቃሚዎች የዘላቂ ኑሮ ዋስትና ስልጠና በዚህ ወር እንደሚጀመር ተገለፀ። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ከድህነት ለማውጣት የከተሞች የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ከዓለም ባንክ በተገኘ 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር እና ከመንግስት 150 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ 450 ሚሊዮን ዶላር ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በትግበራ ላይ ነው። መርሃ-ግብሩ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በ11 ከተሞች የሚገኙ ከ604 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን ያካተታል ተብሏል። እስካሁንም በሁለት ዙር 440 ሺህ 885 ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ከፌዴራል የከተሞች ስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አሰፋ እንደገለፁት የመርሃ-ግብሩ ዋና ዓላማ በከተማ የሚኖሩ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች የተሻለ ገቢ እንዲኖራቸው ማስቻል ሲሆን የከተማውን ልማት ሊደግፉ በሚችሉ የአካባቢ ልማት፣ ፅዳትና የተፋሰስ ስራዎች ላይ ይሰማራሉ። ተጠቃሚዎቹ በዘላቂነት የስራ ባህላቸውን በማሻሻል ከሚያገኙት ገንዘብ እንዲቆጥቡ በማድረግ ወደፊት በተመረጡ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ይደረጋል ብለዋል። በአካባቢ ልማትና ፅዳት ስራ ላይ የተሰማሩ የመርሃ-ግብሩ ተጠቃሚዎችም የሚከፈለው ገንዘብ አነስተኛ ቢሆንም ኑሯቸው ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የመረሃ ግብሩ ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ሙሉ ተፈራ በሰጡት  አስተያየት ''ቤቴ ወስጥ ትንሽ ትንሽ አንጀራ እጋግራለሁ፤ ለውጥም አለው ትንሽ ድጋፍ  ሲያገኝ ሰው መለውጥ  አለበት፤ ግን የሚያረካ አይደለም እና ለጊዜው ደግፎኛል" ነው ያሉት። ''ጥሩ ነው ዳቦ ይገዛል፣ ቡና ይገዛል፣ ስኳር ይገዛል፤ መች አነሰ ይደግፋል '' በማለት የገለጹት ደሞ የምግበ ዋስትና ተጠቃሚ ወይዘሮ እሸቴ አበበ ናቸው፡፡ ተጠቃሚዎቹ ከሐምሌ 2010 ዓም ጀምሮ የስራ ቀናቸውና የሚከፈላቸው ገንዘብ በመቀነሱ ቅሬታ አሰምተዋል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አሰፋ የሚሰሩበት ቀን የተቀነሰው ከመርሃ-ግብሩ ሁለተኛ ዓመት ጀምሮ ወደ ዘላቂ የኑሮ ዋስትና የሚያሸጋግራቸውን የህይውት ክህሎት ስልጠና ስለሚያገኙ ነው ብለዋል። የህይወት ክህሎት ስልጠናው ከመርሃ-ግብሩ ከወጡ በኋላ ህይወታቸውን እንዴት መምራት እንዳለባቸውና የገንዘብ አያያዝ መሆኑን አቶ ሰለሞን ጠቁመዋል። ተሳታፊዎች የራሳቸውን ስራ መፍጠር ወይም ስልጠና ወስደው ተቀጣሪ ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ ይመቻችላቸዋልም ነው ያሉት። በፌዴራል ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና እንደተሰጠና በያዝነው ወር እንደሚጀመር ተናግረዋል። የራሳቸው የንግድ እቅድ አዘጋጅተው የሚሄዱትን ዜጎች ወደ ጥቃቅንና አነስተኛ ገብተው ከአደረጃጀት ጀምሮ ስልጠና፣ ብድር፣ ማምረቻ ቦታና የገበያ ትስስር እንደሚመቻችላቸው ተናግረዋል። በቀን የሚከፈላቸው 60 ብር በቂ ባለመሆኑ የክፍያ ማሻሻያ ለማድረግ በገንዝብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር እየታየ ነው ብለዋል። በመርሃ-ግብሩ ቀጥታ ድጋፍ የሚያገኙ ሰዎች እስከሚጠናቀቅ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል። ቀሪዎቹ 141 ሺህ በሶስተኛው ዙር በሚቀጥለው ዓመት ተጠቃሚ መሆን ይጀምራሉ። መርሃ-ግብሩን ውጤታማ ለማድረግ የ10 ዓመት መርሃ-ግብር የተዘጋጀ ሲሆን በ972 ከተሞች 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ከድህነት ወለል በታች ያሉ ዜጎች እንዳሉ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም