የኦሮሚያ ክልል የአፋን ኦሮሞ ስርዓተ ትምህርት አዘጋጀ

103
አዲስ አበባ ሀምሌ 14/2010 የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የአፋን ኦሮሞ ስርዓተ ትምህርት አዘጋጀ። ትናንት ምሽት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በተገኙበት ስርዓተ ትምህርቱን ያዘጋጁት ምሁራን መጽሃፍቱን በይፋ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ አስረክበዋል። ስርዓተ ትምህርቱን ካዘጋጁት መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አለሙ ኃይሉ እንደሚሉት አሁን የተዘጋጀው መጽሃፍ ሙሉ በሙሉ ከበፊቱ የተለየ ነው። አፋን ኦሮሞን እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚጠቀሙና ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የሚማሩ ልጆች እንደሚማሩበት የተዘጋጀው ስርዓተ ትምህርት ዋናው ትኩረቱ መጻፍና ማንበብ ላይ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት ስራ ላይ የነበረው ስርዓተ ትምህርት መናገርና ማዳመጥን ማዕከል ያደረገና የስነ ልሳን ሳይንሱን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ አልነበረም ይላሉ። በዚህም በተለይ በክልሉ የሚገኙ አብዛኛው የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች አፋን ኦሮሞን መጻፍና ማንበብ እንዳልቻሉ በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል። ስርዓተ ትምህርቱን ካዘጋጁት መካከል አንዱ የሆነው የወለጋ ዩኒቨርሲቲው አቶ ፍቃዱ ቀናአ  የተዘጋጀው ማስተማሪያ መጽሃፍ “አሁን ያለንበትን ዘመን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው'' ይላሉ። በተለይ ደግሞ አሁን የክልሉ ህጻናት አፋን ኦሮሞ መገናኛ ብዙሃንን እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂን የሚተዋወቁበት በመሆኑ ይህን ሊመጥን የሚችል ስርዓተ ትምህርት ነው የተዘጋጀው ብለዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በበኩላቸው አዲስ ስርዓተ ትምህርት ማዘጋጀት ያስፈለገው ልጆች ቋንቋውን ሲማሩ እግረ መንገዳቸውን የክልሉን ነባራዊና ሁለንተናዊ ማንነት ማወቅ እንዲችሉ ነው ብለዋል። ይህ ስርዓት ትምህርት ጥቅም ላይ የሚውለው በክልሉ ውስጥ ብቻ ሳይሆን አፋን ኦሮሞን እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋ በሚጠቀሙ ክልሎችም ጭምር መሆኑን አስረድተዋል። እነዚህም አማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን፣ ሃረሪ ክልል፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የቋንቋው ተናጋሪዎች የሚማሩበት ስርዓተ ትምህርት መሆኑን ጠቁመዋል። ለስርዓተ ትምህርቱ ዝግጅትና በቀጣይም የመጽሃፍት ህትመት፣ የመምህራን ስልጠና ለማከናወን 100 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ስርዓተ ትምህርቱን ያዘጋጁት ምሁራን ለሌሎች የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ምሳሌ የሚሆንና ለትውልድ የሚተላለፍ ስራ ሰርተዋል ይላሉ። “እናንተ በእዚህ ስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ላይ የተሳተፋችሁ ምሁራን ምስጋና ብቻ ሳይሆን ትልቅ ክብር ይገባችኋል'' ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሌሎች ምሁራንም ለመሰል ስራዎች ተባባሪ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። የክልሉ መንግስት ተብትኖ ያለውን እውቀት አሰባስቦ ልማት ላይ ለማዋል የማስተባበር ስራ የሚሰራ በመሆኑ ምሁራን ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም