በመተከል ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም ውሳኔ ተላለፈ

44

ታህሳስ 18/2013(ኢዜአ) በመተከል ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ማዕከል ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ ብሔራዊ ኮሚቴ ውሳኔ አሳለፈ።

የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ማዕከል ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ ብሔራዊ ኮሚቴ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በህግ ማስከበር ሂደቱ ለተከሰቱ ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውሶች ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ተግባራትን ለመገምገም መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

ኮሚቴው ባካሄደው ስብሰባ በመተከል ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም ውሳኔ አሳልፏል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴው የዕለቱ ተቀዳሚ አጀንዳዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ እርዳታ የማዳረስ ተግባራትን ገምግሟል።

እንዲሁም በትግራይ ክልል እና አጎራባች የአማራና አፋር ክልሎች ህግ ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ በኋላ ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ዜጎችን በዘላቂነት የመልሶ የማቋቋም ተግባራት ሂደትንም ገምግማል።

በሰላም ሚኒስቴር የሚመራው የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን፣ እና ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭ አካላትን የያዙ ቡድኖች በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር ክልሎች እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን እንደሚገኙ ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በቡድኖቹ የተጠናቀሩ የየዕለት ተግባራት ሪፖርቶችና የኮሚቴው አባላት አመራሮች በቦታው ተገኝተው ባደረጓቸው የመስክ ምልከታ ላይ ተመስርቶ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጡም ተገልጿል።

በብሄራዊ አደጋ ስጋት አስተዳደር ኮሚሽን አስተባባሪነት በመተከል ዞን በቅርቡ በተመሰረቱት ካምፖች ለሚገኙ ወገኖች የዕለት ደራሽ እርዳታ ማከፋፈሉ እንደቀጠለ ሆኖ በተጨማሪም በርካታ የዕለት ደራሽ እርዳታ የያዙ የጭነት መኪኖች ወደቦታው መንቀሳቀሳቸውን ተጠቅሷል።

ኮሚቴው በመተከል ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ተግባራት ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም ባሳለፈው ውሳኔ በሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች የሚመራ የአመራሮችና ባለሙያዎች ግብረ ኃይል በቦታው ተገኝቶ ለማስተባበር እንዲሁም እንደየአስፈላጊነቱ አመራርና ውሳኔ ለመስጠት ወደ መተከል ዞን መጓዙም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም