በጋምቤላ የውጭ ምንዛሬ ፍሰቱ እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ ባንኮች ገለጹ

4157

ጋምቤላ ሀምሌ 14/2010 ዶላር አከማችተው የያዙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ወደ ባንክ በመሄድ እንዲመነዝሩ መንግስት ባስተላለፈው መልዕክት መሰረት የውጭ ምንዛሬ ፍሰቱ እየጨመረ መምጣቱን በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ባንኮች ገለጹ።

በከተማው ቀደም ሲል ተስፋፍቶ የነበረው የጥቁር ገበያ እንቅስቃሴም እየቀነሰ መምጣቱን ባንኮቹ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሰለ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት መንግስት ያስተላለፈውን መልዕክት ተከትሎ ዶላር ለመመንዘር ወደ ባንኩ የመጡ ደንበኞች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው።

ባንኩ ይህን ታሳቢ በማድረግ በቅርንጫፎቹና በሆቴሎች አካባቢ ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ ጭምር ደንበኞች ወደ ባንኩ እንዲመጡ የመቀስቀስ ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለውጭ ምንዛሬ አገልግሎት ብቻ የሚውል የአንድ መስኮት አገልግልት በመስጠት ላይ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

ላለፉት አምስት ቀናት ወደ ባንኩ በመምጣት ዶላር የሚመነዝሩ ደንበኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በቡና ባንክ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሙሉዓለም ናቸው።

ቀደም ሲል በጋምቤላ ከተማ የጥቁር ገበያ በመስፋፋቱ ምክንያት ዶላር ለመመንዘር ወደ ባንኩ የሚመጡ ደንበኞች እንዳልነበሩ አስታውሰው ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ከሚጠበቀው በላይ በርካታ ደንበኞች ወደባንኩ መጥተው የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በዳሽን ባንክ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ኃይሉ በበኩላቸው ዶላር ለመመንዘር ወደ ባንኩ የሚመጡ ደንበኞች ፍሰት ከቀን ወደቀን እየጨመረ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ቀደም ሲል ከውጭ አገር ይላክላቸው የነበረውን ዶላር በጥቁር ገበያ ሲመነዝሩ የነበሩ ግለሰቦች ሳይቀር የጥቁር ገበያ አማራጭ እያጡ በመምጣታቸው በባንክ እንዲላክላቸው የባንክ አድራሻ በብዛት እየወሰዱ መሆናቸውን አስረድተዋል።