የበጎ አድራጎት ማኀበሩ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው 934 ሴቶችና ህጻናት ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ

54

ባህርዳር፣ ታህሳስ 17/2013(ኢዜአ) አጋር ኢትዮጰያ በጎ አድራጎት ማህበር በባህር ዳር ከተማ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው 934 ሴቶችና ህጻናት ወደ ማዕከሉ በማስገባት ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

ማህበሩ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የመገናኛ ብዙሃንና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለማገዝ ትኩረት እንዲሰጡ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

በማህበሩ የባህር ዳር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉጎጃም ተክሉ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ድጋፍ የተደረገላቸው ሴቶችና ህጻናት ከፖሊስና ሌሎች ተቋማት በትክክል ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑ ተረጋግጦ የተላኩ ናቸው።

ወደ ማዕከሉ ከመጡት ውስጥም 820 የተለያየ አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና 114 በአስገድዶ መደፈር የተወለዱ ህጻናትን መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከተደረገላቸው  ድጋፍ ውስጥ  የምግብ፣ መጠጥ፣ መጠለያ ፣ህክምና፣ የስነ ልቦና፣ የህግና  ክህሎት ሥልጠና እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

በተጨማሪ በልብስ ስፌት፣ ፀጉር ስራ፣ ምግብ ዝግጅትና ሌሎች ሙያዎች በማሰልጠን ለእያንዳንዳቸው 20 ሺህ ብር የስራ ማስጀመሪያ በመመደብ በዘላቂነት ሰርተው እራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ መደረጉንም ሥራ አስኪያጇ ጠቁመዋል።

በዚህም ከስጋት ነፃ ሆነው የሚኖሩበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ  ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤  የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን  ባለሙያዎችም አጥፊዎችን በማጋለጥና ህብረተሰቡን በማስተማር ሊያግዙ ይገባል ብለዋል።

በአማራ ክለል ሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ቢሮ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ባለሙያ አቶ አስናቀ ለወየ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃትት ከግለሰብ አልፎ በማህበረሰብ ደረጃ ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀበላ የፈረመችና በህገ መንግስቱ  ለሴቶች ሁለንተናዊ መብት መከበር ቢደነገግም በአስተዳደር መዋቅሩ ባለው ክፍተት እስካሁን ችግሩን መቀነስ አልተቻለም ብለዋል።

የሃይል ጥቃት ዘላቂ የስነ ልቦና፣ የጤናና ሌላም ተጽዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ  የመገናኛ ብዙሃን  ባለሙያዎች ችግሩን ለማስወገድ  በዘገባ ስራቸው የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ባለሙያ ገነት ጥበቡ እንዳለችው፤ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የማስቆም ጉዳይ ለአንድ ወገን የሚተው አይደለም።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በመቀናጀት የህብረተሰቡን አስተሳሰብና አመለካከት ለመለወጥ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ጠቁማለች።

የኪነ ጥበብ ባለሙያ አቶ ከፍያለው እሸቴ በበኩሉ፤ በክልሉም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰሩ የኪነ ጥበብ ስራዎች የሴቶችና የህጻናት ጥቃትን ለማስቀረት በሚያስችል መልኩ መቃኘት አለባቸው ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ጾታዊ ጥቃትን ለማስወገድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ በሙያቸው የድርሻቸውን ለመወጣት በጋራ ቃል ገብተዋል።

ከታህሳስ 15/2013ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ  የኪነ ጥበብና መገናኛ ብዙሃን  ባለሙያዎች  ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም