በመጪው ክረምት ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ሀገር ውስጥና በጎረቤት ሀገራት ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው

62

አዳማ፤ታህሳስ 17/2013( ኢዜአ)በመጪው ክረምት ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ሀገር ውስጥና በጎረቤት ሀገራት ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ መጪው ክረምት ለመትከል የተቀደው የችግኝ ዝግጅት ዙሪያ  ከአስሩ ክልሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ እየመከረ ይገኛል።

በምክክር መድረኩ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ  ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ  በየነ እንደገለጹት መጪው ክረምት ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በሀገር ውስጥና በጎረቤት  ሀገራት ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በተለይ ከተከላ መሬት ልየታ ጀምሮ የችግኝ ዝግጅት በሀገር ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን  አመልክተው ፣ ስራውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ ሰፊ  ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋት ለጎረቤት ሀገራት ለማድረስ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት  ከስድስት ክልሎችና ከስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም  ከሀገራት አካባቢያዊ ስነ ምህዳር ጋር የሚስማሙ ችግኞች በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ አስታወቀዋል።

"ባለፈው ዓመት በችግኝ ተከላው የታየው ርብርብ በእንክብካቤው በመድገም ልፋታችን  ለውጤት እንዲበቃ ማስቻል አለብን" ብለዋል።

አሁን 15 በመቶ ላይ ያለው የሀገሪቱ የደን ሽፋን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 ወደ 30 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፣ የአባይ ሸለቆን በቀርከሃ ደን ከመሸፈን ጀምሮ የተለያዩ ተፋሰሶችን የማልማት ስራ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል  ገልጸዋል።

ዝግጅቱ ከችግኝ ጣቢያዎች ጀምሮ የዛፍ ዘር አቅርቦት፣የተከላ ቦታ ልየታና ባለቤት  የማበጀት፣የፕላስቲክ አቅርቦት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  በኮሚሽኑ የደን ሴክተር ልማት አስተባባሪና ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ ኮሚቴ ሰብሳቢ  ዶክተር  ተፈራ መንግስቱ ናቸው።

"ችግኝ በማፍላት ረገድ ዝግጅቱ በጥሩሁኔታ እየሄደ ነው ፤ የተከላ ቦታ ላይ ውስንነት  የሚታይ በመሆኑ በትኩረት እንሄድበታለን" ብለዋል።

በዚህም ከ6 ቢሊዮን በላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን የዛፍ ችግኞች ለማዘጋጀት የቅድመ  ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ዶክተር ተፈራ ተናግረዋል።

የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛው በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች የውሃ ግኝት እየተሻሻለ  ከመሆኑንም ባለፈ  የደረቁ ወንዞችና  የተመናመኑ የወንዞች  ፍሰት እየተመለሰ  ይገኛል  ብለዋል።

የዝናብ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ  መሆኑን ጠቁመው ይህም  በተፈጥሮ ሀብት  ልማት ላይ በተከናወነው ስራ የተገኘ ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ በዋናነት የሚጎዳው የውሃ ሀብቱን ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይ ጎርፍና ተከታታይ ድርቅ  በማስከተል በተፈጥሮ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎች የውሃ ሀብቱን  አስተማማኝ ለማድረግ፣ ግድቦችን ጨምሮ የውሃ መሰረተ ልማቶች በደለል እንዳይሞሉ፣ የገፀ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ማሳደግ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም