ሴቶች ጎልተው እንዳይወጡ የሚያደርጉ የአስተሳሰብ ችግሮችን በማስወገድ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል - የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም

76


ታህሳስ 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) ሴቶች ወደፊት ጎልተው እንዳይወጡ የሚያደርጉ የአስተሳሰብ ችግሮችን በማስወገድ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ።


በደቡብ ኦሞ ዞን በጅንካ ከተማ ሴቶችን በኢኮኖሚው ተጠቃሚ የማድረግ ንቅናቄ መድረክ በሀይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከፊንላንድ ኢምባሲ በተገኘ ድጋፍ ተዘጋጅቷል።


በመድረኩ ላይ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ፣ የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር አውቲ ሆሎንፒያና እና ባለቤታቸው ተገኝተዋል።


የመድረኩ ዓላማ ሴቶች ከወንዶች እኩል በልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ በባለቤትነትና በግንባር ቀደምነት እንዲንቀሳቀስ ንቅናቄ መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።


በዚህ ወቅት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከበደ ሳህሌ፤ ፋውንዴሽኑ በዞኑ ያለውን የመልማት ክፍተቶች ለመሙላት እና የዞኑ ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፕሮጀክት ቀርፆ ሊሰራ በመምጣቱ ምስጋና ችረዋል።


ፋውንዴሽኑ በዞኑ በትህምርት ጤና እና አካባቢ ጥበቃ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ለሚሰራው ስራ የዞኑ መስተዳድር ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


የሴቶችና ህፃናት ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኦሙድ በበኩላቸው ሴቶችን በማብቃት ረገድ የመጀመሪያው የኢኮኖሚ አቅምን መገንባት በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።


ከዚህ አኳያ የሀይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ያለውን የንቅናቄ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ታሪክ እንድትወጣ መሰረት የጣሉት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬም የህዝቦች ህይወት እንዲሻሻልና እንዲለወጥ በፋውንዴሽናቸው የልማት ስራ እየሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።


በዚህም በሴቶችና ህጻናት፣ በአካባቢ ጥበቃ እና ስራ እድል ፈጠራ የሚሰሩት ስራ የክልሉን ልማት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።


የክልሉ መንግስት ፋውንዴሽኑ ለሚሰራቸው ስራዎች አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።


የፋውንዴሽኑ የቦርድ ሊቀመንበር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ሴቶችን ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አላቆ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ አንስተዋል።


ሴቶች በባህል ሀይማኖት እና ማህበረሰባዊ አሰራሮች ወደ ፊት ጎልተው እንዳይወጡ የሚያደርጉ የአስተሳሰብ ችግሮች ተፈተው ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም