በትግራይ ክልል ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ድጋፍ ይደረጋል---የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

61

አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ አስፈለጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በትግራይ ክልል የህወሃት ጁንታ በፈጠረው ችግር በተከናወነው ህግ የማስከበር ሂደት ሥራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ በክልሉ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

በውይይቱ መንግስት በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በመፍታት አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ለማድረግ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የብረታ ብረትና ኬሚካል ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ዮሐንስ ድንቅአየሁ እንደገለጹት የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

ዘርፉን ወደ ነበረበት በመመለስ ያለውን አስተዋጽኦ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በክልሉ ጁንታው በፈፀመው የአገር ክህደት በተወሰደው የህግ ማስከበር በርካታ ኢንዱስትሪዎች ሥራቸውን ማቆመቸውን ጠቁመው፣ እነዚህን ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

"ኮሚቴው የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ህግ ከማስከበር ሥራው ጎን ለጎን ኢንዱስትሪዎች ላይ ሊገጥም የሚችለውን ችግርና መፍትሔ ሲያጠና ቆይቷል" ብለዋል።

እያንዳንዱን ኢንዱስተሪ ሥራ ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን የመለየት ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

በጁንታው እኩይ ተግባር በከፊልና ሙሉ በሙሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ኢንዱስትሪዎች መንግስት በተቻለ አቅም መልሶ እንዲያቋቁማቸውም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።

መንግስት ሁኔታዎችን ካመቻቸ በፍጥነት ወደ ሥራ የመግባት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አቶ ዮሐንስ በምላሻቸው የድጋፍ ጥያቄ እያቀረቡ ላሉ ድርጅቶች እንደጥያቄው አግባብ ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ነው የገለጹት።

በቀጣይም ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ችግሮች ለሚስተዋሉባቸው ተቋማት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

ጉዳት ለደረሰባቸው አምራች ኢንዱስትሪዎችም የውጭ ምንዛሬ እና የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲያገኙ እንዲሁም ከተቋማት ቅድሚያ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አሰራር ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

በክልሉ 93 ከፍተኛ እንዲሁም 6 ሺህ 965 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም