የምክር ቤቱ አባላት ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር በነጻነት ሊሰሩ ይገባል ... አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

46

ጂግጅጋ፤ ታህሳስ 16/2013(ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አባላት ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር በነጻነት ሊሰሩ እንደሚገባ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የዴሞክራሲ ተቋማትም ነጻነትና ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

አፈ-ጉባኤው ይህን ያሉት ዛሬ በሶማሌ ክልል ጂግጅጋ ከተማ በተጀመረው የፌዴራል ዴሞክራሲ ተቋማት የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በውይይቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀጣይ አምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፣ የኢትዮጵ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለን ጨምሮ የብዙሃን መገናኛ ተቋም አመራሮች ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎቹ  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች መካከል በልዩ ሁኔታ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች መከበር ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ንዑስ ኮሚቴ ይቋቋም የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

የሚወጡ ሕጎች ቶሎ የሚሻሩ እንዳይሆኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር መደረግ አለበት ብለዋል።

በዜጎች እንዲመለሱ የሚነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያን አቅም ባገናዘበ መልኩ ተተንትነው ለአስፈጻሚ አካላት የሚቀርቡበት አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባም ነው ተሳታፊዎቹ ያነሱት።

የምክር ቤቱ አባላት ከፓርቲ ተጽእኖ እንዴት ነጻ ሆነው ሊሰሩ ይችላሉ የሚል ጥያቄም ተነስቷል።

የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው ባለመስራታቸው ምክንያት የሚፈለገው የዴሞክራሲና ሰላም መምጣት አለመቻሉም በተሳታፊዎች ተነስቷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤው ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ስትራቴጂክ እቅዱ ምክር ቤቱ ከተለመደው አሰራር ወጥቶ ሃላፊነቱን በተሻለ መልኩ እንዲያከናውን ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ከስትራቴጂክ እቅዱ የሚቀዱ መመሪያዎችና የአሰራር ስርዓቶች እንደሚዘጋጁ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ የምንችለው ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ሲቻል ነው ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ከዚህ አንጻር የምክር ቤቱ አባላት ነጻ ሆነው ተቋማትን መቆጣጠርና መደገፍ አለባቸው ብለዋል።

ተቋማትም ይህን በመገንዘብ ነጻነታቸውንና ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው በህግ የተሰጣቸውን ሃላፊነት መከወን እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

በኢትዮጵያ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ለምክር ቤቱ ነጻነት ጥሩ እድል እንደፈጠረም ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ከዚህ በፊት በፓርቲ አጥር ውስጥ ሆነው ስራቸውን ሲያከናውኑ እንደነበርና ከዚህ አጥር ውጭ የሚያፈነግጥ አባል ከፍተኛ እንግልት ይደርስበት እንደነበርም አስታውሰዋል።

አሁን ላይ አባላቱ ከማንም ነጻ በመሆን ለወከላቸው ህዝብ ጥያቄ መከበር እየሰሩ እንደሆነና ይህንንም አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በቀጣይ ምክር ቤቱን ተደራሽና አሳታፊ ለማድረግ የሚያግዙ አሰራሮች እንደሚዘረጉም አክለዋል።

የፌደራል ዴሞክራሲ ተቋማት የምክክር መድረክ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም