በጸጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የንግድ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የተወሰደ እርምጃ የለም - የወላይታ ሶዶ ተጎጂዎች

77
ሶዶ ሀምሌ 14/2010 በወላይታ ሶዶ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው የንግድ ተቋማት መልሶ  ለማቋቋም የተወሰደ እርምጃ ባለመኖሩ መቸገራቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተጎጂዎች ገለጹ፡፡ የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በከተማዋ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተጎዱ ግለሰቦችን ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከተጎጂዎች መካከል በከተማው በአልባሳት ንግድ የተሰማሩት አቶ ጌታሁን ሃይሌ እንዳሉት በጸጥታው ችግር ምክንያት ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት ወድሞባቸዋል፡፡ በከተማዋ መሠል የጸጥታ ችግር ታይቶ እንደማያውቅ የገለጹት አስተያየት ሰጪው ጉዳዩ ባልታሰበ ሰዓት በመከሰቱ ንብረታቸውን ማዳን እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስራቸው ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ከነቤተሰቦቻቸው ለችግር መዳረጋቸውን ጠቅሰው ''ከተማ አስተዳደሩ መልሶ እንደሚያቋቁማቸው ቢገልጽም ተግባራዊ የተደረገ ነገር የለም'' ብለዋል፡፡ በጫማና ጃንጥላ ጥገና የተሰማሩት አቶ ታከለ ባሳ በበኩላቸው በጸጥታው ችግር ከ25 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት በመውደሙ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚሁ ሙያቸው ሰርተው በሚያገኙት ገቢ የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦቻቸው ለከፋ ችግር እንደተዳረጉ ገልጸው መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ታረቀኝ ባዳቾ በከተማዋ ባልተለመደ መልኩ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በሰው ህይወት እንዲሁም በግለሰቦችና በመንግስት ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ተጎጂዎችን ለማቋቋምና የከተማውን ሠላም ወደነበረበት ለመመለስ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ ሲሆን የወደመውና የተዘረፈው ንብረት እየተለየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለመልሶ ማቋቋሚያው ከወላይታ ዞንና ከተማ አስተዳደር 3 ሚሊዮን ብር መመደቡን የገለጹት አቶ ታረቀኝ ለተጎጂ ወገኖች በጉዳታቸው መጠን እንደሚከፋፈል አስታውቀዋል፡፡ የተዘረፉ ንብረቶችን ከፖሊስ ጋር በመሆን የማስመለስ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ በከተማው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር 85 የንግድ ቤቶች ሲወድሙ ከጉዳይ ጋር በተያያዘ ከ250 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም