ግምታቸው ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

55

ደሴ ታህሳስ 16/2013 (ኢዜአ) ባለፉት አምስት ወራት ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዙን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮምሽን የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ አስታወቀ። 

ቅርንጫፉ በኮንትሮባንድ መከላከል ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ  በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የቅርንጫፍ የህግ ተገዥነት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ከፍያለው ቢያዝን በወቅቱ እንደገለጹት  የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ  እየተባባሰና አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

ቅርንጫፉ በ2010 ዓም  የያዛቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ግምት 18 ሚሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰው  በ2012 አም የተያዙ እቃዎች ግምት ወደ 83 ሚሊዮን ብር ማደጉን ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት አምስት ወራት ብቻ ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡

በወራቶቹ ከተያዙት መካከል የፋብሪካ ምርቶች፣ ልባሽ ጨርቆች፣ በቱሪስት ስም ሊገቡ የነበሩ ዘመናዊ ተሸከርካሪዎች፣ የጦር መሳሪያዎችና በመንግስት ብቻ ሊገቡ የሚችሉ የድጎማ ምርቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በኮንትሮባንድ እንቅሰቃሴው ከተሳተፉ መካከል 23ት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጎ ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮንትሮባንድ በሀገር ኢኮኖሚዊ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት ድርጊቱን በዘላቂነት ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ቅንጅት ለማጠናከር የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል ።

የደቡብ ወሎ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ በበኩላቸው ዞኑ ከተለያዩ ክልሎች ጋር ተጎራባች በመሆኑ ለኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እንደ መሸጋገሪያ እያገለገለ መሆኑን ጠቁመዋል።

"የባለድርሻዎች ቅንጅት ክፍተትና የአመራር አካላት ቸልተኝነት ድርጊቱ እንዲባባስ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው" ብለዋል ።

ኮንትሮባድ ለጤና ስጋት፣ ለዋጋ ንረት፣ ለመንግስት ገቢ መቀነስ፣ ለስርዓት አልበኝነት መስፋፋት መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

"የቅንጅት ክፈተት የኮንትሮባድ እንቅስቃሴው እንዲባባስ ከማደረጉም ባለፈ የፍርድ ሂደቱ እንዲዛባና እንዲጓተት እያደረገ ነው"ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ጀንበሩ ካሳ ናቸው።

በቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃና  መረጃ ማግኘት ባለቻል ብቻ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በጉዳዩ ላይ የተያዙ ከ500 በላይ ሰነዶች ሳይቋጩ በእንጥልጥል ላይ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በውይይት መደረኩ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ የስራ ኅላፊዎች ፣የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች፣ የጸጥታና የፍትህ አካላት ተሳትፈዋል

በመድረኩ በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድርጊቱን ለመከላከል የራሱን ኅላፊነት ወሰዶ እንዲሰራ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን ባለድርሻዎች በቅንጅት በሚሰሩባቸው  ሁኔታዎች ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም