በአሜሪካ የሚደረገው ጉባኤ ለዳያስፖራው አንድነትና ህብረት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል - አስተባባሪ ኮሚቴው

53
አዲስ አበባ ሀምሌ 13/2010 በአሜሪካ የሚደረገው የኢትዮጵያውያን ህዝባዊ ጉባኤ ለዳያስፖራው አንድነትና ህብረት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጸ። ኮሚቴው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የልኡካን ቡድን ከሐምሌ 21 ቀን 2010 ጀምሮ በአሜሪካ የሚያደርገውን ጉብኝት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የአቀባበሉ ስነስርዓትና የዝግጀቱ ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ላይ በዋሽንግተንና በአካባቢዋ ያሉ የኢትዮጵውያንና ኢትዮጵያን አስመልክተው በስፋት የሚሰሩ ሚዲያዎች ተሳታፊ ነበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩትና "የጥላቻና የልዩነት ግንብን አፍርሰን የፍቅርና የአንድነት ድልድይ እንገነባለን" በሚል መሪ ሃሳብ በዋሽንግተን  ዲሲ የሚካሄደው የኢትዮጵያውያን ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን ዳያስፖራው በንቃት እየተሳተፈ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል። ጉባኤው በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ህዝባዊ መነቃቃት በማጠናከር ለዳያስፖራው አንድነትና ህብረት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል። የኮሚቴው የሚዲያ ተጠሪ አቶ አቤል ጋሸ ጉባኤውን በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሚዲያ በቀጥታ ለማስተላለፍ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸው፤ ይህን በምን መልኩ መሆን አለበት በሚለው ላይ ከሚዲያዎች ጋር ምክክር እንደሚደረግ ጠቁመዋል። 'ይህ የኢትዮጵያውያን ልዩ ጊዜ ነው' ያሉት አቶ አቤል፤ ጉባኤው የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ሁሉ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል። ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ከአምስት መቶ በላይ አስተናጋጆች መዘጋጀታቸውንም አቶ አቤል ጠቁመዋል። በጉባኤው በክፍያ የምግብና መጠጥ መስተንግዶ እንደሚኖር ገልጸው፤ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የሚኖሩ ታክሲ አሽከርካሪዎች ኢትዮጵያውያን ተሳታፊዎችን ወደ ጉባኤ አዳራሹ በነጻ እንዲያጓጉዙ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም