ፍርድ ቤቱ በዶክተር አዲሳለም ባሌማ ላይ የ13 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

67

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዶክተር አዲሳለም ባሌማ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የ13 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

የህወሓት የጥፋት ቡድን ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶክተር አዲሳለም ባሌማ ዛሬ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።

ዶክተር አዲስ አለም ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ መርማሪ ፖሊስ በጠየቀው መሰረት 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጥቶት ነበር።

መርማሪ ፖሊስም በነዚሁ ቀናት ውስጥ ተጠርጣሪው በምዕራብ ወለጋ ዞን ከሚገኘው የኦነግ ሸኔ አባላት ጋር ግንኙት ሲፈጥሩ እንደነበር መረጃዎች ማግኘቱን ገልጿል።

ተጠርጣሪው "የኦነግ ሸኔ አባላትን ካልተያዙት የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር በማገናኘት የገንዘብና የቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት ሲያደርግ የነበረ መሆኑን ደርሼበታለው" ብሏል።

የኦነግ ሸኔ አመራሮችን አዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት መሥሪያ ቤት አካባቢ በሚገኘው ቢሮ በመሰብሰብ ተልዕኮ ይሰጧቸው እንደነበር ማስረጃ ማሰባሰቡንም ፖሊስ ገልጿል።

የአማራና የኦሮሞ ወጣቶችን ለማጋጨት ከህወሓት አመራሮች ጋር ተልዕኮ በመስጠት ሲንቀሳቀሱ የነበረ መሆኑንም እንዲሁ።

ከኦሮሚያ ከልል ወጣቶችን በመመልመልና በማደራጀት ወደ ትግራይ ክልል ወስደው በማሰልጠን በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ አመጽና ሁከት እንዲያስነሱ ወጣቶቹን ማሰማራታቸውን የሚያመላከት መረጃ መገኘቱንም ፖሊስ አስረድቷል።

"ከህወሓት አመራሮች ጋር ተልዕኮ በመስጠት እንዲሁም ከተለያዩ ሰዎች የተሳሳተ መረጃ እየተቀበሉ በራሳቸው ድረ-ገጽ በተለያዩ የውጭ አገራት ለሚኖሩ ሰዎች ሲያሰራጩ እንደነበረም መረጃ ተሰባስቧል" ብሏል ፖሊስ። 

ከእዚህ በተጨማሪ ከተጠርጣሪው መኖሪያ ቤትና እጃቸው ላይ የተገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ለምርመራ መላኩን  ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

መርማሪ ፖሊስ በተፈቀደለት ጊዜ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን ገልጾ አሁንም የቀሩ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የ14 ቀናት እንደሚያስፈልገው ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

"በተለይ ተጠርጣሪው ዋና የወንጀል አድራጊ መሆናቸውና ከወንጀሉ ሥፋትና ውስብስብነት አኳያ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ያስፈልገኛል" ሲል መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል። 

ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ጊዜ ውስጥ  13 ተጨማሪ ቀናት ፈቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም